ደቡብ አፍሪካ በኦን ላይን የአውራሪስ ቀንድ ሽያጭ ጨረታ ልታደርግ ነው

ደቡብ አፍሪካ የኦንላይን የአውራሪስ ቀንድ ሽያጭን ልታከናወን መሆኑ ተገለጸ ።

የዓለም 80 በመቶ የሚሆኑ አውራሪሶች በዚህችው አፍሪካዊት ሃገር እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

ደቡብ አፍሪካ የበርካታ አውራሪሶች መኖሪያ በመሆኗ ትልቋ የአውራሪሶች መንደር በመባልም ትታወቃለች፡፡

በፕላኔታችን ከሚገኙ አውራሪሶች መካከል 80 ከመቶ የሚሆኑቱ በዚህችው አፍሪካዊት ሃገር ይገኛሉ፡፡

የእነዚህ አውራሪሶች ቀንድ ደግሞ እጅግ ተፈላጊ በመሆኑ የሚሸጡበት ዋጋም እጅግ የተጋነነ ሲሆን አንድ ኪሎ ግራም የሚመዝን የአውራሪስ ቀንድ በህገወጥ ገበያ እስከ 60 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ይሸጣል፡፡

ይህ አሃዝ አንድ ሚሊዮን ሶስት መቶ ሰማኒያ ሺህ የኢትዮጲያ ብር ሲሆን ይህም የአውራሪስ ቀንድ ዋጋ ከወርቅና ከኮኬይንም በላይ እጅግ ውድ መሆኑን ያሳያል፡፡

ምንም እንኳ ደቡብ አፍሪካ ከ20 ሺህ በላይ አውራሪሶች መኖሪያ ብትሆንም የህገወጥ ነጋዴዎችን ኪስ ከማድለብ ባለፈ ለሀገሪቱ ይህ ነው የሚባል ጥቅም ሳያበረክት ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡

በመሆኑም አለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚሳተፍበትና ሃገሪቱም ጠቀም ያለ ገቢ የምታገኝበት ይሆናል የተባለለትን የኦን ላይን ሽያጭ ጨረታ ማዘጋጀት አስፈልጓታል፡፡

ይህን ቴክኖሎጂ መጠቀም ህገ ወጥ የአውራሪስ ቀንድ ንግድን ለማስቀረትም ትልቅ ሚና ይኖረዋል ነው የተባለው፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ የአውራሪስ ቀንድ ሽያጭ መከልከሉን ተከትሎ የደቡብ አፍሪካ ባለስልጣናት ስጋት ስላደረባቸው የኦንላይን ሽያጭ ጨረታውን ለማገድ ፈልገው የነበረ ቢሆንም የፕሪቶሪያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግን ፈቃድ ሰጥቷል፡፡

ይህን ተከትሎም ከያዝነው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ በቴክኖሎጂ እየታገዘ የአውራሪስ ቀንድ ሽያጭ ጨረታው የሚካሄድ ይሆናል፡፡

የፕሪቶሪያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ እንደገለጸው የሃገሪቱ ባለስልጣናት ኦን ላይን ጨረታውን ለማገድ ፈልገው የነበረ ቢሆንም ባለፈው ሚያዚያ ወር የተሸሻለውን ህግ መሰረት በማድረግ ፍርድ ቤቱ ፈቃድ ሰጥቷል፡፡

ይህም የአውራሪሶችን ጭፍጨፋና ህገወጥ ንግዱን በተወሰነ መልኩ ይቀንሰዋል ብሎ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ያምናል ብሏል አቃቤ ህጉ፡፡

ህገ ወጥ ንግዱና የአዳኞች ጭፍጨፋ እስካሁን የእንስሳቱን ደህንነትና የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ሲጎዱ መቆየታቸውንም አያይዘው ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ቅርብ ጊዜያት አውራሪሶቹ በከፍተኛ ሁኔታ አዳኞች እያሳደዷቸው በመሆኑ ምቾት እየተሰማቸው እንዳልሆነም ተነግሯል፡፡

በመሆኑም በእስያ ገበያዎች በጣም ተፈላጊ የሆነውን የአውራሪስ ቀንድ ህጋዊ በሆነ መንገድ ለገበያ ማቅረቡ የእንስሳቱን ጭፍጨፋ ለመቀነስ ያግዛል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዘመናዊ መንገድን የተከተለው የኦን ላይን ጨረታ ንግድ የተሻለ መንገድ ነውም ተብሏል፡፡( ምንጭ: ሲጂቲኤን)