የመንግሥታቱ ድርጅት በሱዳን ነዋሪዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት መበራከቱን ገለጸ

በደቡብ ሱዳን እርዳት አቅራቢዎች እና በነዋሪዎች ላይ የሚደረርሰው ጥቃት እየተበራከተ መምጣቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ ።

በደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ግጭቶች መበራከታቸውን ተከትሎ በንጹሃን ዜጎች እና በእርዳታ አቅራቢ ሰራተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ድብደባ እና ግድያ እንዲቆም የመንግስታቱ ድርጅት በጥብቅ አሳስቧል፡፡

በዚች በዓለም አዲስ የሆነችው ሀገር እ.ኤ.አ ህዳር 2013 ላይ ከተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት ጀምሮ በተያዘው አመት የሞቱትን 15 ሠራተኞች ጨምሮ እስካሁን ከ80 በላይ የሚሆኑ የእርዳታ ሠራተኞች በደቡብ ሱዳን ህይወታቸው አልፏል፡፡ 

የሰብአዊ እርዳታው አስተባባረሪ የሆኑት ሴርጌ ቲሶት አለም አቀፍ የሰብአዊ ቀን ላይ እንዳሉት አሁንም ቢሆን ንጹሃን ዜጎች እና የእርዳታ ሰራተኞች ላይ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚደርሱ ጥቃቶች እየተበራከቱ እንደመጡ መመስከር የሚቻል ሲሆን ይህ ሁኔታ ግን በፍጹም በቀጠል የለበትም ብለዋል፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት እንዳለው ከሆነ ጥቃቶች በተለያዩ መንገዶች እየተፈጠሩ ሲሆን በብዛት ግጭቶችን ተከትሎ ተሸከርካሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ሌሎች ንብረቶች የተዘረፉ ሲሆን ለእርዳታ ሊቀርብ የተዘጋጀ በርካታ ቶን ምግብም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ጠፍተዋል፡፡ይህም ደቡብ ሱዳንን ዕርዳታ ለማቅረብ ከባድ የሆነች የአለምችን ሀገር አድርጓታል፡፡

የእርዳታ ሰጪዎች ላይ ጥቃት በሚደርስበት ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የምግብ፣ የመጠጥ ውሀ፣ የጤና እና የትምህርት አገልግሎት ፈላጊዎች ከባድ ችግር ውስጥ በመግባት ለሞትም እንደሚዳረጉ ሁሉም ሰው ማስተዋል አለበት ሲሉ ቲሶት አሳስበዋል፡፡

የእርዳታ ስራውን በደቡብ ሱዳን በተገቢው እንድናከናውን ይረዳን ዘንድም ማንኛውም የታጣቂ ኃይል አባላት ንጹሃን ዜጎችን፣ ሰራተኞችን እና የእርዳታ ማእከላትን ኢላማ ያደረገ ጥቃት ከመፈጸም በመቆጠብ እንደውም ተገቢውን ከለላ ሊያደርጉላቸው ይገባል ሲሉ የእርዳታው አስተባባሪ ጠይቀዋል፡፡ ( ምንጭ:  ራድዮ ታማዙጅ)