ኢንቨስት ኢን አፍሪካ በጋና ለሚገኙ አነስተኛ የንግድ ኢንተርፕራይዞችን ምርታማ ለማድረግ 500 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አደረገ

ኢንቨስት ኢን አፍሪካ የተባለ ድርጅት በጋና የሚገኙ አነስተኛ እና መካከለኛ የንግድ ኢንተርፕራይዞችን ምርታማ ለማድረግ 500 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ድርጅቱ ፓርትነር ፑል ከተባለ የኦን ላይን ገበያ ኩባንያ ጋር በመሆን ከ15 በላይ ሃገራት የሚገኙ ሻጮችን እና ገዢዎችን በማገናኘት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ለትርፍ ያልተቋቋመው ኢንቨስት ኢን አፍሪካ የተሰኘው ድርጅት በአፍሪካ የቢዝነስ እድልን ለማስፋፋት የተለያዩ ሥራዎችን ይሠራል፡፡

ድርጅቱ በአፍሪካ ውስጥ በትላልቅ ኩባንያዎች እና በአነስተኛ የንግድ ተቋማት  መካከል የንግድ ልውውጥ እንዲኖር ለማድረግ የግብዓት፣ የንግድ ሥራ ማሻሻያ ሥልጠናዎች እና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የጥቃቅን እና አነስተኛ የንግድ ተቋማትን አቅም ማሳደግ ዋናው ዓላማ አድርጎ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ ነው፡፡

ድርጅቱ በጋና የጥቃቅን እና አነስተኛ የንግድ ተቋማትን ለማሳደግ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ሃገሪቷን በአነስተኛ እና በመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ይበልጥ ውጤታማ እንድትሆን የሚረዳ የ500 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ የድጋፍ ፕሮግራሙም ለቀጣይ 4 ዓመታት እንደሚቆይ ነው የተገለጸው፡፡

ፕሮግራሙ ተግባራዊ ሲደረግ በተመረጡ የኢኮኖሚ ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ 100 ሺ ለሚሆኑ ዜጎች ተጨማሪ የሥራ እድልን ይፈጥራል ነው የተባለው፡፡

አነስተኛ እና መካከለኛ የንግድ ተቋማት ተደራሽ ለመሆን ጠንክረው ቢሰሩም የፋይናንስ፣ የአቅም እና የገበያ ትስስር ችግር በስፋት እንደሚያጋጥማቸው የኢንቨስት ኢን አፍሪካ ድርጅት የጋና ቅርንጫፍ ዳይሬክተር ሚስተር ክላረንስ ናርቴይ ገልጸዋል፡፡

አሁን ግን ድርጅታቸው በሀገሪቱ ውስጥ በአነስተኛና በመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የተሰማሩ የንግድ ድርጅቶች አቅማቸውን ማዳበር የሚያስችል አቅም እንዲኖራቸው በእነዚህ ሶስት ቁልፍ ነገሮች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ከቻለ በዘርፉ የሚስተዋሉትን ችግሮች ከመቅረፉም ባለፈ የኢኮኖሚ እና የሥራ እድል እንደሚፈጥርም ተናግረዋል፡፡

ኢንቨስት ኢን አፍሪካ ከኢኮ-ባንክ እና የጋና ንግድ ባንክ ጋር በመተባበርም በጋና ለሚገኙ ኢንተርፕራይዞች የ1 ሚሊዮን ዶላር ብድር ተጠቃሚ አድርጓል፡፡

ኢንተርፕራይዞቹ ምቹ የገበያ ትስስር እንዲኖራቸውም ድርጅቱ የመጀመሪያውን የኦንላይን ገበያ ተግባራዊ የሚያደርግ ሲሆን ፓርትነር ፑል የሚል ስያሜም ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ የኦንላይን ግብይት ላይም 15 በላይ ሃገራትን ውስጥ ያሉ ከ1ሺህ 500 አቅራቢዎች ከገዢዎች ጋር የሚያገናኝ ይሆናል ተብሏል፡፡

 

በአፍሪካን ፓርትነር ፑል ላይ ለሚመዘገቡ በጋና የሚገኙ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከቀጥተኛ እና ከተዘዋዋሪ አገልግሎት እና ምርቶች ላይ የ150 ሚሊዮን ዶላር ተጠቃሚ የሚሆኑበት እድል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የኢኮኖሚ ተደራሽነት እንዲሰፋም ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመስራት በ10 ሴክተሮች ውስጥ ከ30 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውን የገለፁ ሲሆን በዚህም ሃገሪቷ ኦኮኖሚ ላይ ተሳታፊ የሚያደርግ ማህበራዊ እውቅና ማግኘት ችለናል በማለት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።