የአፍሪካ ሀገራት ነጻ የንግድ ቀጠናን ተግባራዊ ለማድረግ ተስማሙ

የአፍሪካ ሀገራት ነጻ የንግድ ቀጠናን ተግባራዊ ለማድረግ ተስማሙ። ስምምነቱ የሀገራቱን ምጣኔ ሀብት በእጅጉ የሚያሳድግና በአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለዉን የንግድ ልዉዉጥ በእጥፍ ሊያሳድግ የሚችል ስለመሆኑም ተነግሯል።

ስምምነቱን 54 የአፍሪካ ሀገራት ሲፈርሙ ኤርትራ ብቸኛዋ እምቢታዋን የገለፀች ሀገር ሆናለች፡፡

የአፍሪካ ሀገራት ከአራት አመታት ብርቱ ክርክርና ዉይይት በኋላ ባለፈዉ መጋቢት ወር ላይ በስምምነት የተቋጨዉ የአፍሪካ ሀገራት ነፃ የንግድ ቀጠናን የመመስረት እቅድ ትላንት በናሚቢያዋ መዲና ኒያሚ በተካሄደዉ 35ኛዉ አስቸኳይ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በ54ቱ ሀገራት መሪዎች ፊርማ መደምደሚያዉን አግኝቷል።

በዘንድሮዉ የመሪዎቹ ጉባኤ ወሳኝና የአህጉሪቱን ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር ያጠናክራሉ የተባሉ ዉሳኔዎች ተላልፈዋል።

ነፃ የንግድ ቀጠናዉ 1.3 ቢሊየን የሚሆኑትን የአህጉሪቱ ዜጎች የሚያስተሳስርና 3.4 ትሪሊየን ዶላር የሚገመት ምጣኔ ሀብታዊ ቀጠና የሚፈጥር እንደሚሆን ታምኖበታል። በርግጥ አዲሱ ስምምነት የአህጉሪቱን ቀጣይ የልማት ትንሳኤ የሚያበስር እንደሚሆንም ይጠበቃል።

መሪዎቹ በትላንትናዉ ዉሳኔያቸዉ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ጋና የንግድ ቀጠናዉ መቀመጫ እንድትሆን ዉሳኔ አስተላልፈዋል።

የአለም የንግድ ተቋም ከ25 አመታት በፊት በፈረንጆቹ 1994 ከተመሰረተ ወዲህ በግዙፍነቱ ሁለተኛ ነዉ የተባለለት አዲሱ የአፍሪካ ሀገራት ነፃ የንግድ ቀጠና፣ በአህጉሪቱ ሀገራት መካከል የንግድ ትስስርን የሚያጠናክር፣ የአቅርቦት ሰንሰለቶችን የሚያሰፋና የአህጉሪቱን ምጣኔ ሀብት በእጅጉ የሚያሳድግ እንደሚሆን ታምኖበታል።

በስምምነቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና የግብፁ ፕሬዝደንት አብዱልፈታህ አልሲሲ አፍሪካዊያን እርስ በእርስ በመደጋገፍ አህጉሪቱን ለማልማት ከስምምነት በመድረሳችን የአለም አይኖች ሁሉ ወደ አፍሪካ እንዲዞሩ ሆኗል ብለዋል።

የስምምነቱ መፈረም በአህጉረ አፍሪካ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ለማስመዝገብና የህዝቦቿን የዘመናት የልማት ህልም ለማሳካት ብሎም ኑሯቸዉንም በዘላቂነት ለመቀየር ፅኑ መሰረትን የሚጥል ስለመሆኑም አልሲሲ አንስተዋል።

የአፍሪካ ሀገራት እርስ በእርሳቸዉ የሚያደርጉት አህጉር አቀፍ የንግድ ትስስር ከሌሎች አህጉራት ጋር ስነፃፀር እጅጉን ዝቅተኛ እንደሆነ ይነገራል። ለአብነት በፈረንጆቹ 2017 የእስያ ሀገራት 59 በመቶ የአዉሮፓ ሀገራትም ቢሆኑ 69 በመቶ ያክሉን የንግድ ልዉዉጥ ያደረጉት እርስ በእርሳቸዉ ነዉ።

በአፍሪካ ሀገራት በአንፃሩ በአህጉሪቱ የነበረዉ የእርስ በእርስ የንግድ ልዉዉጥ ከአህጉሪቱ አመታዊ የዉጭ ንግድ 17 በመቶ ያክሉን ብቻ የሚሸፍን ነበር። ይህ መሆኑ ደግሞ ሌሎች የንግድ ቀጠናዎች ባለፉት አስርት አመታት በጋራ በመስራታቸዉ ያስመዘገቡትን ምጣኔ ሀብታዊ ስኬት አፍሪካዊያን ሀገራት እንዳይጋሩት አድርጓቸዉ ቆይቷል።

በእርግጥ አፍሪካዊያን ተመሳሳይ የንግድ ትስስሮችን ላለመፍጠራቸዉ እንቅፋቶች እንደነበሩ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያነሳሉ። በተለይም እንደ መንገድ የመሳሰሉ የመሰረት ልማት ዝርጋታዎች አናሳ መሆን፣ አሳሪና ነፃ ያልሆኑ የድንበር ላይ አሰራሮች፣ ስር የሰደደ ሙስናና በተለያዩ የአህጉሪቱ አከባቢዎች የሚስተዋሉ አለመረጋጋቶችና የሰላም እጦት ዋነኞች ምክኒያቶች ናቸዉ።

54 የስምምነቱ ፈራሚ ሀገራት በአብዛኞቹ ምርቶቻቸዉ ላይ የቀረጥ ቅነሳ ለማድረግ ወስነዋል። ይህ ደግሞ እንደ አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ግምት የአሁኑ ነፃ ንግድ ቀጠና መመስረት የአህጉሪቱን ንግድ ከ15 እስከ 25 በመቶ እንዲያድግ ያስችላል። ከዛም በዘለለ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች፣ በተለይም እንደ ሙስናና ዉስብስብ አሰራሮች የሚወገዱ ከሆነ የአህጉሪቱ ንግድ ከተባለዉም በላይ በእጥፍ ኢያድግ ይችላል ተብሎ ይገመታል።

በእርግጥ በተለያዩ የአፍሪካ ክፍሎች ተመሳሳይ አላማን ያነገቡ እንደነ ECOWAS፣ EAC፣ SADC እና COMESA የመሳሰሉ ቀጠናዊ ተቋማት የነበሩ ቢሆንም ከምስራቅ አፍሪካዉ EAC ዉጭ ቀሪዎቹ ተቋማት ይህ ነዉ የሚባል የስኬት ታሪክ የላቸዉም። በተለይም በሀገራት መካከል ያለዉ የሀሳብ መለያየት ለዚህ ዋነኛዉ ምክኒያት ነዉ።

የአሁኑን ስምምነት ስኬት ይነፍጉታል ከተባሉት ጉዳዮችም የሀገራት የሀሳብ መለያየት አንዱ ነዉ። በተለይም እንደነ ናይጄሪያ ለመሳሰሉት ባለ ግዙፍ ምጣኔ ሀብትና ኢኮሚያቸዉ በነዳጅ ላይ ለተመሰረተ ሀገራት የአሁኑ ስምምነት እምብዛም የጎላ ጥቅም የለዉም። ይህም ለናይጄሪያና መሰሎቿ የስጋት ምንጭ ሆኗል።

እንደነ ደቡብ አፍሪካ የመሳሰሉት ሀገራት በአንፃሩ ከስምምነቱ የተሻለ ተጠቃሚዎች እንድሚሆኑ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ገምተዋል።

እናም በሀገራት መካከል ያለዉን የተጠቃሚነት ልዩነት መቅረፍና ልዩነቱን ማጥበብ የአዲሱ ስምምነት ፈታኝ ስራ ይሆናል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል።