ኡጋንዳ ከ1ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን መቀበሏን ገለጸች

ኡጋንዳ ባለፉት 12 ወራት ብቻ  የተቀበለቻቸው ስደተኞች ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ መድረሳቸው ተመልክቷል ፡፡

ይህም ቀደም ሲል ከመላው ዓለም ስደተኞችን በከፍተኛ ቁጥር ሲቀበሉ ለነበሩት የአውሮፓ ሀገራት እፎይታን ፈጥሯል እየተባለ ነው፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ግሪክና ቱርክ ነበሩ በርካታ ስደተኞን በመቀበል በዓለም ከሚገኙ ሀገራት ጫና   የስደተኞች ጎርፍ በርትቶባቸው  የነበረው፡፡

በዚህም ምክንያት የታዋቂ ጋዜጦች የፊት ገፅ ማድመቂያ ፤ የበርካታ መገናኛ ብዙሃንም ርዕስ የነበረው እንደነ ግሪክና ቱርክ ያሉት ሀገራት ይህን ያህል ስደተኞችን ተቀብለው እያስተናገዱ ይገኛሉ የሚለው ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡

በሚሊየን የሚቆጠሩ ስደተኞች ሶሪያን ጨምሮ በመካከለኛው ምስራቅ በእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሱ ከሚገኙ ሀገራት ስደተኞች ወደ አውሮፓ ሲፈልሱ መቆየታቸውም የቅርብ ጊዜ የሚታወስ  ነው፡፡

ስደተኞችን በመቀበል ረገድ እያከናወነች ያለችውና ለዚህ ስራዋ ግን ብዙም ዕውቅና ያልተቸራት ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኡጋንዳ በታሪኳ ደርሳበት የማታውቀውን የስደተኞች ቁጥር ለማስተናገድ ተገዳለች ይላል የኤቢሲ ኒውስ ዘገባ፡፡

ባለፉት 12 ወራት ብቻ ሀገሪቱ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ ስደተኞችን ተቀብላ ለማስተናገድ ተገዳለች፡፡

ይህ ማለት በተጠቀሰው ዓመት ግሪክም ሆነ ቱርክ ብሎም የትኛውም ሀገር ይህን ያህል ቁጥር ያለው ስደተኛን በአንድ ዓመት ውስጥ  አላስተናገደም ማለት ነው፡፡

ጦርነት ፣ ድርቅና ግጭትን በመሸሽ በየቀኑ ከ2 ሺህ በላይ ዜጎች ደቡብ ሱዳንን ከመሳሰሉ ጎረቤት ሀገራት ድንበር አቋርጠው የኡጋንዳን  ይገባሉ ።

በተለይም በእርስ በእርስ ግጭት ስትታመስ በቆየችው ደቡብ ሱዳን  የዕለት የምግብ እርዳታ የሚያሻቸው ሰዎች ቁጥር ከ6 ሚሊየን ማሻቀቡ ነው የተነገረው፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሪፖርት እንደሚጠቁመው በደቡብ ሱዳን ከ276 ሺህ በላይ ህዝብ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጋለጠ ነው፡፡

በደቡብ ሱዳን ከ5 ሺህ ሰዎች አንዱ በከፍተኛ የምግብ እጥረት ሳቢያ በየቀኑ የሚሞት ሲሆን÷ ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ህዝብ 30 በመቶ የሚሆነውም ለከፍተኛ የምግብ እጥረት የተጋለጠ ነው፡፡

ይህን ተከትሎ ከደቡብ ሱዳንየሚመጡ ስደተኞች ቁጥር ከማሻቀቡ የተነሳ ቀደም ሲል በዓለም ካርታ ላይ ከነጥብ ብዙም ያልዘለለ ስፍራን የያዘውና በኡጋንዳ ሰሜናዊ ግዛት የሚገኘው የፓላብክ መንደር አሁን ላይ ከ170 ሺህ በላይ ስደተኞች መጠለያ ለመሆን ተገድዷል፡፡

ሌላውና ቀደም ሲል በስደተኞች በመጣበቡ ምክንያት ተዘግቶ የቆየው ቢዲ ቢዲ የተሰኘው መንደርም መጠጊያ ያጡ ከ250 ሺህ ስደተኞችን በእቅፉ ይዞ ይገኛል፡፡

የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ኡጋንዳ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች በማስተናገድ አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነች መሆኗን ጠቅሰው፣አለምአቀፉ ማህበረሰብ አስፈላጊውን ሰብዓዊ ድጋፍ ለስደተኞች እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

የኡጋንዳ መንግስት በበኩሉ ሀገሪቱ ለምታከናውነው የሰብዓዊ ድጋፍ እንቅስቃሴዎች ከ8 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አስታውቋል፡፡

ስደተኞችን  በመቀበልና በማስተናገድ  ኢትዮጵያና ኡጋንዳ ተጠቃሽ ሀጋራት ናቸው፡፡