ሞሱሉን መልሶ ለመገንባትና ነዋሪዎቿን ለማቋቋም አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል

ከአይ ኤስ ነፃ የወጣችውን ሞሱልን መልሶ ለመገንባትና ነዋሪዎቿን ለማቋቋም አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል ተባለ፡፡

ከተማዋን መልሶ ለመገንባት አንድ ቢሊዮን ዶላር፤ ነዋሪዎቿን ለማቋቋም ደግሞ 126 ሚሊዮን ዶላር እንደሚስፈልግ ነው የተገለፀው፡፡ አይ ኤስን ከኢራቅ አቅራቢያ ማጥፋት ቀጣዩ የኢራቅ የቤት ሥራ መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡

ከአሸባሪው አይ ኤስ ነፃ የወጣችው የሰሜን ኢራቅ ከተማ ሞሱል አሁን ሰላምና መረጋጋት እንደሰፈነባት ተመልክቷል ፡፡

እኤአ ከ2014 ዓመት ጀምሮ በአሸባሪው ድርጅት አይ ኤስ መዳፍ ሥር የወደቀችውን ታሪካዊቷን ሞሱልን ለማስለቀቅ ከፍተኛ ትግል ተደርጓል፡፡

የኢራቅ ጦር ከተማዋን ከጽንፈኛው ቡድን ለማስለቀቅ ባለፈው ጥር ወር ባወጀው ዘመቻ  ምስራቅ ሞሱልን ማስለቀቅ መቻሉ ይታወሳል ፡፡

ከሁለት ወር በፊት ደግሞ ምዕራባዊ ሞሱልን ከአይ ኤስ ለማስለቀቅ በአሜሪካ መራሹ ጥምር ኃይል በመታገዝ የተፋፋመው ዘመቻ የአሸባሪውን አቅም በማዳከም ሞሱል ነፃ መውጣቷ መሆኑን የሚገልፅ ዜና በመላው ዓለም ተሠራጨ፡፡               

ጥምር ኃይሉ አቅሙን በማጠናከር ከሶስት ዓመት በኋላ በአይ ኤስ ላይ ድልን ተቀዳጀ፡፡ የሞሱል ነፃ የመውጣትን ብስራት የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይደር አል አባዲ  አውጀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር አባዲ ለጦር ኃይሉ ምስጋናቸውን ለኢራቃውያንም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትን አስተላልፈዋል፡፡

ታሪካዊቷ ሞሱል በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎቿን በሞት ተነጥቃለች፡፡ 920 ሺ የሚደርሱት ደግሞ ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለዋል፡፡

አምስት ሺ የሚደርሱ ህንፃዎች የፈራረሱ ሲሆን 450 ያህሉ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ብሏል የመንግስታቱ ድርጅት፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀው ከተማዋን መልሶ ለመገንባት አንድ ቢሊዮን ዶላር፤ የተፈናቀሉትን ነዋሪዎች መልሶ ለማቋቋም ደግሞ 126 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡

በኢራቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ ሊዜ ግራንዴ በሞሱል ከአይ ኤስ ጋር የነበረው ጦርነት ቢያበቃም ሰብዓዊ ድጋፉ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡

ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት ዜጎች ባዶ እጃቸውን መቅረታቸውን የጠቆሙት ግራንዴ ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያና የጤና አገልግሎትን ለማሟላት አስቸኳይ ድጋፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ እናም ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

አሁን ጊዜው ሞሱልን መልሶ መገንባት ነው ተብሏል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይገባል፡፡

የሞሱልን ነፃ መውጣት ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የፈረንሳዩን ኢማኑኤል ማክሮንን ጨምሮ የተለያዩ የዓለም መሪዎች ለኢራቁ አቻቸውና ኢራቃውያን  የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሞሱልን ማስለቀቅ አይ ኤስን ድባቅ መምታት ባለመሆኑ ጽንፈኛውን ቡድን የመዋጋቱ ጥረት በቀጣይ የሚጠናከር እርምጃ ነው ብላለች ኢራቅ፡፡ አይ ኤስን ከኢራቅ አቅራቢያ ማራቅና ማጥፋት ቀጣዩ የቤት ሥራ መሆኑም ነው የተገለፀው፡፡