የአሜሪካ አየር ኃይል በሰነዘረው የአየር ላይ ጥቃት የአልሻባብ ቁልፍ ሰው ተገደለ

የአሜሪካ መከላከያ ኃይልና የሶማሊያ መንግስት በጋራ በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት የአሜሪካ አየር ኃይል በድንገት በከፈተው የአየር ጥቃት የአሸባሪ ቡድኑ ወሳኛ ኮማንደር ተገድለዋል፡፡

በሞቃዲሾ የአልሻባብ ዋና ጉዳይ አስፈጻሚ  ሆኖ ለረጂም ዓመታት ያገለገለው ኮማንደር አሊ ሞሃመድ ሁሴን በዚህ ጥቃት መገደሉን ነው የሶማሊያ ደህንነት ባለስልጣናት የተናገሩት፡፡

የሶማሊያ የመረጃ ሚኒስትር አብዱራህማን ኦመር ኦስማን እንደገለጹት ሟቹ  ኮማንደር አሊ ሞሃመድ ሁሴን በዋናነት በቅጽል ስሙ አሊ ጀበል የሚታወቅ ሲሆን የአሸባሪ ቡድኑም ቁልፍ ሰው ነበርም ብለዋል፡፡

ከአሜሪካ አየር ኃይል ጋር በመተባበር ይህን ወታደራዊ ተልዕኮ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ ትዕዛዝ መሥጠታቸውንም ሚኒስትሩ አያይዘው ገልጸዋል፡፡ 

በሞቃዲሾ አቅራቢያ በተወሰደው የአየር ላይ የቦምብ ጥቃት የአሸባሪ ቡድኑን ትላልቅ ተልዕኮዎችን ለበርካታ አመታት ሲፈጽምና ሲያስፈጽም የቆየውን ሰው ተግድሏል ብለዋል፡፡

በዚህ የአየር ላይ ጥቃት በንጹሃን ዜጎች ላይ የደረሰ ምንም አይነት ጉዳት እንደሌለም ተጠቁሟል፡፡

በጥቃቱ ላይ ከሶማሊያና አሜሪካ በተጨማሪ ሌሎችም አካላት የተካተቱ ሲሆን  አልሻባብ  በቅርቡ በሶማሊያ ወታደሮች ላይ ለሰነዘረው ጥቃት ምላሽ ለመሥጠት የተወሰደ እርምጃ ነውም ተብሏል፡፡

የሶማሊያ ደህንነት ሚኒስትር ሃሰን ሁሴን ሞሐመድ በበኩላቸው አሸባሪ ቡድኑ በታችኛው የሸበሌ አካባቢና ቡላ-ባኒን መንደሮች ይንቀሳቀስባቸው የነበሩ ሁለት ተሸከርካሪዎች የጥቃቱ ኢላማ ነበሩ ብለዋል፡፡ 

ከጥቃቱ ጋር የተያያዙ ተጨማሪ መረጃዎችን በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርጉም የደህንነት ሚኒስትሩ አያይዘው ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ቀደም አልሻባብን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት የአሜሪካ አየር ሃይል ተከታታይ የአየር ጥቃት በተለይም በደቡባዊ የሶማሊያ ክፍል ሊያከናውን እንደሚችል መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የሶማሊያ የሽግግር መንግስት በአሁኑ ወቅት ከአሸባሪ ቡድኑ አጸፋዊ ምላሽ እንዳይወሰድበት በከፍተኛ የደህንነት ስራ ተጠምዶ ይገኛል፡፡ (ምንጭ:ቪኦኤ)