በኬንያ ምርጫ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ አሸነፉ

ኬንያ ስታካሄድ የነበረው ምርጫ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ማሸነፋቸውን የአገሪቱ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ ።     

ኬኒያ ስታካሄድ የነበረዉ ምርጫ በትላንትናው እለት ዉጤቱ ይፋ የሆነ ሲሆን፥ ነባሩ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከ14 ነጥብ 8 ሚሊየን መራጮች መካከል የ8 ሚሊየን 43 ሺህ 470 ወይም 54 ነጥብ 3 በመቶ የሚሆነውን ድምፅ በማግኘት አሸንፈዋል፡፡

ከፍተኛ ግምት አግኝተው የነበሩት ተቀናቃኙ ራዪላ ኦዲንጋ ደግሞ የ 6 ሚሊየን 643 ሺህ 819 መራጮችን ወይም 44 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆነውን ድምፅ ያገኙ ቢሆንም ተሸንፈዋል፡፡

ኬንያ ከዚህ በፊት ባደረገቻቸው ምርጫዎች በየጊዜው አመፆች መነሳታቸዉን ተከትሎ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በኤሌክትሮኒክስ መንገድ የመራጮችን ድምፅ የሰበሰበች ቢሆንም አሁንም ከአመፅ የፀዳ ምርጫ ማከናወን አልቻለችም፡፡

ይህን ተከትሎም ዉጤቱን በፀጋ መቀበል ያቃታቸዉ ኦዲንጋ ማክሰኞ እለት የተካሄደዉ ምርጫ ዉጤቱ መጭበርበሩን በመናገራቸዉ በተለያዩ የኬኒያ ከተሞች ደጋፊዎቻቸዉ አመፅ አስነስተዋል፡፡

አመፀኞቹም ከፖሊሶች ጋር ግብግብ ውስጥ በመግባታቸው በከፍተኛ ሁኔታ አመፁ መባባሱ እየተነገረ ነው፡፡

በዚህም አመፅ የተነሳ እስካሁን 5 ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ ሁለት የሚሆኑት በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በተነሳው ግርግር የተገደሉ ናቸው ፡፡