አሜሪካ ለቬንዙዌላ ፕሬዚዳንት ታዛዥ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ ጣለች

አሜሪካ ለቬንዙዌላዉ ፕሬዝዳንት ታዛዥ በሆኑ ስምንት የሀገሪቱ ባለስልጣናት ላይ የማዕቀብ ውሳኔ አሳለፈች፡፡

ሀገሪቱ ይህን ውሳኔ ያሳለፈችው ባለፈው አርብ በቬንዙዌላ የረቀቀውና ለፕሬዝዳንቱ ሙሉ ኃላፊነት ይሰጣል የተባለው ህገ መንግስት ተግባር ላይ ከዋለ በኋላ በሀገሪቱ ቀውስ እንዲፈጠር ምክንያት በሆኑ ባለስልጣናት ላይ ነው፡፡

አሁን አሜሪካ ያሳለፈችው የማዕቀብ ውሳኔ የቬንዝዌላን ፖለቲካኞችና የፀጥታ ኃይል ኃላፊዎችን ዒላማ ያደረገ እንደሆነ ነው እየተነገረ ያለው፡፡

ባሳለፍነው አረብ ቬንዝዌላን ሶሻሊስት ፓርቲ አጋሮቻና መሪው ፓርቲ ስብሰባ አካሂደው ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ መሠረት በሥልጣን ላይ ያለው የሶሻሊስት ፓርት የሀገሪቱን ህገ መንግስትን በአዲስ መልክ ለማርቀቅ የሚያስችል እድል ይሰጣል፡፡

ከዚህም ውጭ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሩ በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ረገጣ እያካሄዱ ስለመሆናቸው ጠንካራ ትችት ሲሰጡ የነበሩት የሀገሪቱ ዓቃቢ ህግ ከስልጣናቸው እንዲነሱ አድርጓል፡፡

በሀገሪቱ የተቃዋሚ ድምጾችም እንዳይሰሙ ማዱሩ እየወሰዷቸው ያሉ ተግባራት ተደራራቢና ከህዝቡም ይሁንታን ያስገኙላቸው አይደሉም፡፡

የማዱሩ ታማኝ እንደሆነ የሚነገረው የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍር ቤትም በዋና ከተማዋ ካራካስ ግዛት ስር የምትገኝ ከተማ ከንቲባ የነበሩትን ራሞን ሙቻቾ ከስልጣናቸው እንዲነሱና ለ15 ወራት በእስር እንዲያሳልፉ አድርጓል፡፡

ይህ ውሳኔ የመጣው ደግሞ ሰውየው በከተማዋ በፕሬዝዳንት ማዱሩና በሥርዓቱ ላይ ያነጣጠሩ ተቃውሞች አይለው ሲቀጥሉ አልተቆጣጠሩም ተብለው ነው፡፡

አሜሪካ አሁን በስምንት የሀገሪቱ ፖለቲከኞችና በፀጥታ ኃይሎች የማዕቀብ ውሳኔ ያስተላለፈችው በዚህ ሁሉ ሂደት የፕሬዝዳንት ማዱሩን ውሳኔ አሜን ብለው ስላጸደቁ ነው፡፡

አሜሪካ እነዚህ ባለስልጣናት ማዱሩንና ሥርዓቱን በመደገፍ ህዝቡ ለተቃውሞ እንዲወጣ ምክንያት ናቸው ትላለች፡፡

አሜሪካ ከወር በፊት ተመሳሳይ ማዕቀብ በአስራ ሶስት የሀገሪቱ ባለስልጣናት ላይ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡    

አሜሪካ ይህን ማዕቀብ ስታሳልፍ እየሽቆለቆለ ያለውን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እየደገፈ የሚገኘው የነዳጅ እንዲሁም የኃይል ዘርፍን አልነካችም፡፡

አሁን አሜሪካ እየወሰደች ያለው በሀገሪቱ ባለስልጣናት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ ብቻውን ትርጉም የሌለውና በቂ አለመሆኑን ነው ምሁራኑ የሚተቹት፡፡

ከግለሰቦች ማዕቀብ ባለፈ ጠንከር ያለ የኢኮኖሚ ማዕቀብ በሀገሪቱ  ላይ ማሳለፍ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

ከባለፈው ሚያዚያ ወር ጀምሮ በቬንዝዌላ በደረሰ ቀውስ 125 ሰዎች ሂወታቸውን አጥተዋል  ሲል የዘገበው ሮይተርስ ነው፡፡