የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፍትሃዊ እንደነበር ኢጋድ አስታወቀ

የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ግልጽ እና ሁሉን አሳታፊ እንደ ነበር  የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት( ኢጋድ) ገለጸ።

በአምባሳደር ተወልደ ገብረመስቀል የተመራ 18 አባላት ያሉት የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን  ትላንት ምሽት የተጠናቀቀውን  የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በታዛቢነት ተሳትፏል።

ቡድኑ በምርጫው ወቅት የምርጫ ኮሮጆዎች ሲከፈቱ፣ የምርጫ ሂደቱና  የድምፅ ቆጠራውን  በንቃት መታዘቡን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመላክቷል።

በምልከታውም ምርጫው የአገሪቱን  ሕገ-መንግስት መሰረት ባደረገ መልኩ ወጣቶችን ፣ ሴቶችንና አዛውንቶችን ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ያሳተፈ እንደነበር በመግለጫው አብራርቷል ።

የኬንያ የምርጫ ሀላፊዎች  ምርጫውን  ግልጽና ተጠያቂነት በሰፈነበት መልኩ ማዘጋጀታቸውን እንደታዘበ ድርጅቱ አስታውቋል።

ለምርጫው አጠቃላይ ደህንነት በቂ የፀጥታ ሀይል መመደቡንም ጠቁሟል።

ታዛቢ ቡድኑ መራጩ ህዝብ  በሰላምና በትግስት ምርጫውን ሲያካሂድ እንደዋለ ገልጾ፤የምርጫ ጣቢያዎችና ማዕከላት ለመራጮች  አመችና ግልጽ በሆኑ ቦታዎች መመቻቸታቸውን አብራርቷል ።

የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የኬንያን ህዝብና በምርጫው የተሳተፉ ፓርቲዎች  ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ያደረጉትን አስተዋጽኦ አድንቋል። 

በምርጫው የተሳተፉ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የኬኒያን ህዝብ ድምጽ እንዲያከብሩም መልእክቱን አስተላልፏል(ኢዜአ )።