አሜሪካ ለግብጽ የምታደርገውን ድጋፍ መቀነሷ ተመለከተ

አሜሪካ  በግብጽ እያደገ የመጣውን  የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተከትሎ ለግብጽ የምታደርገውን  ድጋፍ  መቀነሷን   ገለጸች ።                     

በግብጽ የሚስተዋለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተከትሎ አሜሪካ ለግብጽ ከምታደርገው ድጋፍ አስከ ሶስት መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ቀንሳለች ተብሏል፡፡

ግብፅ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላት መልካም የሚባል ግንኙነት ለዚህ ቅጣት እንደዳረጋት አየተነገረ ይገኛል፡፡

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በግብጽ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳለ የሚያምን ሲሆን ይህንንም አጥብቆ ይቃወማል፡፡

ይህን ተከትሎም ልዕለ ሃያሏ ሃገር አሜሪካ ለግብጽ ከምታደርገው የኢኮኖሚ ድጋፍ ላይ 96 ሚሊዮን ዶላር ስትቀንስ ለወታደራዊ ድጋፍ ከምታደርግላት ገንዘብ ላይ ደግሞ 195 ሚሊዮን ዶላሩን ወደ ካዚናዋ ለመመለስ ወስናለች፡፡

እንደ አሜሪካ ባለስልጣናት ገለጻ ከሆነ አሜሪካ የግብጽን ወታደራዊ ኃይል ማጠናከር ለደህንቷ ወሳኝ መሆኑን ብታምንም በግብጽ ያለውን የሰብአዓዊ መብት ረገጣ ግን ፈጽሞ የምትደግፈው ጉዳይ አይደለም፡፡ 

ይህ የአሜሪካ እርምጃ ላለፉት በርካታ ዘመናት የልብ ወዳጇ ሆና ለዘለቀችው አፍሪካዊት ሃገር አጅግ አስደንጋጭ እንደሆነም እየተነገረ ይገኛል፡፡

በመሆኑም ግብጽ መለስ ብላ የሀገር ውስጥ ፖሊሲዋን እንድትፈትሽ ያስገድዳታለል የተባለ ሲሆን ጥሩ ያልሆነው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ታሪኳንም እንድታሻሽል ያስችላታል ተብሎ እንዲጠበቅ አድርጓል፡፡

ግብጽ ላለፉት 30 ዓመታት ከወዳጇ አሜሪካ ብቻ ከሰማንያ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የእርዳታ ገንዘብ  ድጋፍ  አግኝታለች፡፡

ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ግብጽ ይህንን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ካላስተካከለች በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው ግንኙነት ይበልጥ ሊሻክር እንደሚችልም ለግብጹ አቻቸው አብዱል ፈታ አልሲሲ በቅርቡ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

እንደ የአሜሪካው ቁጥር አንድ ተነባቢ ጋዜጣ ኒው ዮርክ ታይምስ ገለጻ  አሜሪካ በግብጽ ላይ የወሰደችው እርምጃ ከባድና ያልተለመደ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈም ግብጽ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላት መልካም ግንኙነት የዶናልድ ትራምፕ በትር እንዲያርፍባት እንዳደረጋት የሚናገሩ አካላት ብቅ እያሉ ነው፡፡

በዋሺንግተን የመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ዳይክተር ሮበርት ሳት ሎፍ እንደሚያምኑት አሜሪካ በግብጽና ሰሜን ኮሪያ መካከል ያለው ግንኙነትን ስላልወደደችው እንጂ በሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ስለተቆጣች ይህን እርምጃ አልወሰደችም፡፡

ግብጽ ከሰብዓዊ መብት ረገጣ ጋር በተገናኘ ከተለያዩ አካላት ወቀሳዎች ሲሰነዘሩባት የቆየች ሃገር ነች ሲል ኒውስ ናው ዘግቧል፡፡