ታንዛኒያ የወባ በሽታ ሥርጭትን ለመቆጣጣር ከ 27 ሚሊዮን በላይ አጎበር ልታሠራጭ ነው

ታንዛኒያ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመቆጣጠር እንዲያስችላት ከ 27 ሚሊዮን በላይ የጸረ-ወባ ትንኝ መድሃኒት የተረጨበት አጎበር በመላው አገሪቱ አካባቢዎች  ልታሠራጭ ነው፡፡

የታንዛኒያ የወባ ስርጭት መቆጠጠሪያ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ቻርለስ ሙዋሊሙ እንደገለጹት በከፍተኛ ፍጥነት አያደገ የመጣውን የወባ በሽታ ለመከላከል ከ27 ሚሊዮን በላይ አጎበሮች በመላ ሃገሪቱ ይሰራጫሉ፡፡

አጎበሮቹ ከአለም አቀፉ የወባ መከላከልና መቆጣጠር ፈንድ እንደተገኙም ሙዋሊሙ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ሚስተር ሙዋሊሙ ገለጻ እያንዳንዱ አጎበር ሶስት ነጥብ አንድ ዶላር የሚያወጣ ሲሆን ለሶስት ተከታታይ አመታት ያገለግላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አንዱ አጎበር ለሁለት አዋቂ ሰዎች የሚበቃ በመሆኑ በስርጭቱ ወቅት ብክነት እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረጋል ብለዋል ሙዋሊሙ፡፡

ከሃያ ሰባት ሚሊዮን አጎበሮች ውስጥ 15 ሚሊዮኑ በዘመቻ የተቀረው 12 ሚሊዮን ደግሞ ከአንድ አመት በታች ለሆኑ ህጻናትና ለነፍሰጡር እናቶች ይሰራጫል ተብሏል፡፡

ይህ ወባን የመከላከልና የመቆጣጠር ዘመቻ በሶስት ክፍሎች የሚከናወን መሆኑን ሙዋሊሙ ጠቁመው ዘመቻው በመጪዎቹ የፈረንጆቹ 2019 እና 2020 ዓመታት ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

ሃገሪቱ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ቆርጣ የተነሳች በመሆኗ በአጎበር ስርጭቱ ወቅት ለሚገጥሙ እጥረቶች በቂ ዝግጅት ማድረጓም ተነግሯል፡፡

ሃገሪቱ የወባ በሽታ ስርጭትን ለመግታት የምታደርገውን ጥረት ከአለም አቀፉ የወባ መከላከልና መቆጣጠር ፈንድ  በተጨማሪ በርካታ  የእርዳታ ድርጅቶች እየደገፉት ይገኛሉ፡፡

ወባን ለመከላከል የሚደረጉትን ጥረቶች  ሁሉም ታንዛኒያዊያን የግልና የአካባቢያቸውን ንጽህና በመጠበቅ እንዲያግዙም ሙዋሊሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡( ምንጭ:ዘኔሽን)