ግብፅ በዩኔስኮ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ አልጀሪያ ድጋፍ እንድትሰጣት ጠየቀች

ግብጽ  በመጪው ጥቅምት ወር ላይ በሚካሄደው  የዩኔስኮ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ  አልጄሪያ ድጋፍ  እንድትሠጣት ጥያቄ  አቀረበች ።

ሁለቱም ሃገራት በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ በአልጄሪያ ተወያይተዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት ( ዩኔስኮ) በየአራት ዓመቱ ድርጅቱን የሚመሩ ኃላፊዎችን ይመርጣል፡፡

በተለይም የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶችን በመሰነድ እውቅና የሚሠጠው ይህው ዓለም አቀፍ ድርጅት ባለፈው መጋቢት ወር ላይ እጩዎቹን በመምረጥ ይፋ አድርጓል፡፡ በሚቀጥለው  ጥቅምት ወር ላይም የዳይሬክተር ጄነራልነት ምርጫውን በይፋ ያካሂዳል፡፡

ድርጅቱ  ለአራት ዓመታት በበላይነት የሚመሩት ዘጠኝ እጩዎችን የመለመለ ሲሆን አዘርባጃን፣ ቬትናም፣ ኳታር፣ ቻይና፣ ጓቴማላ፣ ኢራቅ፣ ሊባኖስ እና ፈረንሳይ ይጠቀሳሉ፡፡ ግብፅ ደግሞ ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር ሆና ታጭታለች፡፡

በፈረንጆቹ ከ1946 ጀምሮ ዩኒስኮን በአባልነት የተቀላቀለችው ጎረቤት ሃገር ግብፅ ስምንት ታሪካዊ ቦታዎቿን በድርጅቱ መዝገብ ላይ ያሰፈረች ሲሆን ቀሪ 33 መስህቦቿንም ለማስመዝገብ በእጩነት አቅርባለች፡፡

ሃገሪቱ ቅርሶቿን ከማስመዝገቧ በዘለለ የቀድሞ ዲፕሎማቷ እና የካቢኔት ሚኒስትሯ ሙሽራ ሃታብን በዳይሬክተር ጄነራልነት እንዲታጩ አድርጋለች፡፡

የአልጀሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር አህመድ ኦያህያ የቀድሞውን የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሀመድ ኢል ኦራቢን ተቀብለው በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ የመከሩ ሲሆን በተለይም ግብፅ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት የዳይሬክተር ጄነራልነት ውድድሯ ላይ አልጀሪያ ድጋፍ እንድትሰጣት ጠይቀዋል፡፡  ( ምንጭ: ሚድል ኢስት ሞኒተር)