የኬንያ ተቃዋሚ ፓርላማ አባላት ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የጠሩትን ስብሰባ ተቃወሙ

የኬንያ የተቃዋሚ የፓርላማ አባላት ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አዲሱን ፓርላማ መክፈታቸውን ተቃወሙ፡፡

ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የጠሩትን የፓርላማ አባላት  ስብሰባ ጥሪ  ተከትሎ አብዛኞቹ  የአደሱ ፓርላማ አባላት ስብሰባን አልታደሙም ተብሏል፡፡

የኬንያ ጠቅላይ  ፍርድ ቤት ከወር በፊት በሀገሪቱ የተካሄደውን ምርጫ ውድቅ በማድረጉ ዳግም ምርጫ  በመጭው ጥቅምት ወር ላይ እንዲካሄድ ወሰኗል፡፡

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ያልተለመደ እና ኬንያዊያን ያልጠበቁት ለአሸናፊው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታም ቢሆን እፎይታን ያልሰጠ ነበር፡፡

እንዲያውም ፕሬዝዳንት ኡሁሩ እንዳሉት ዳግም በምርጫ ካሸነፉ የሀገሪቱን የፍርድ ቤት አደረጃጀት እንደሚያስተካክሉም ከውሳኔው በኋላ ተናግረዋል፡፡

አሁን ደግሞ የኬንያ የተቃዋሚዎች ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ  የህዝብ ተወካይዮች  ምክር ቤት አባላትን መሰብሰባቸው ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

የተቃዋሚ አባላቱን ለዚህ ውሳኔ ያበቃቸው  ነጥብ ደግሞ በሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት  ዳግም ምርጫ ሳይደረግ ፕሬዝዳቱ ፓርላማውን የመሰብሰብ ሥልጣን ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በጠሩት የፓርላማው ስብሰባ ላይ የተቃዋሚ የፓርላማ አባላት እንደማይገኙ አስታውቀዋል፡፡

ይልቁንም የፕሬዝዳንት ኡሁሩ ተቀናቃኝ የሆኑትን የራይላ ኦዴንጋን የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ላይ ተሳትፎ እያደረጉ ነው፡፡

ተቃዋሚ የፓርላማ አባላት ይህን ማለታቸውን ተከትሎ ግን ፕሬዝዳንት ኡሁሩ እንዳሉት የትኛውም የተቃዋሚ አባል በፓርላማው መክፈቻ ላይ አለመገኘታቸው ስብሰባውን ከማካሄድ እንደማይቆጠቡ ገልጸዋል፡፡

እሳቸው የሚመሩት የጁቢሊ ፓርቲ አብላጫ የፓርላማ መቀመጫ ስላለው ስበሰባውን ማድረግ እንደሚችሉም አንስተዋል፡፡

ኬንያታ አክለውም አሁንም ስልጣን ላይ ነኝ ስለሆነም በየትኛውም ጊዜ ፓርላማው እንዲሰበሰብ የማድረግ ሥልጣኑ አለኝ ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ አዲስ መንግስት በዚህች ሀገር ላይ እስካልተሰየመ ድረስ በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ መሰረት ፓርላማውን የመሰብሰብ ኃላፊነት አለኝም ነው ያሉት፡፡

እሳቸው አሁን ያካሄዱት የፓርላማ ስብሰባ አንድ ብቻ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የተሳተፈበት እና አመዛኙ ተቃዋሚዎች ግን ያልታደሙበት ነው ተብሏል፡፡

ባሳለፍነው ነሐሴ ወር ፕሬዝዳንት ኬንያታ የሀገሪቱን ጠቅላላ ምርጫ ሀምሳ አራት በመቶ በማግኘት ማሸነፋቸው ተገልጾ ነበረ ፡፡

ይሁን እንጅ ምርጫው ትክክለኛ ሂደቱን አልጠበቀም መባሉን ተከትሎ የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲደገም ወስኗል፡፡

የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በቀጣይ ሳምንት መጨረሻ በፁሑፍ የተደገፈ ማስረጃ በማቅረብ የፕሬዝዳንት ኡሁሩን ማሸነፍ ውድቅ እንዳደረገ እንደሚያስታውቅ ገልጧል፡፡

የፕሬዝዳት ኡሁሩ ተቀናቃኝ ራይላ ኦዲንጋ ይህ ምርጫ እንዲጭበረበር እጃቸውን ያስገቡ የመንግስት ባለስልጣናት ከስልጣናቸው እንዲወገዱ እስካልተደረገ ድረስ በሀገሪቱ የሚካሄደውን ዳግም ምርጫ ደጋፊዎቻቸው እንዲቃዎሙ መልዕክት እያስተላለፉ ነው ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡