በደቡብ ሱዳን መንግሥትና አማጽያኑ መካከል ግጭት መቀስቀሱ ተመለከተ

በደቡብ ሱዳን በመንግስትና አማጽያኑ መካከል ግጭት ተቀስቅሶ እንደነበር የአይን እማኞችን ገለጹ ።

በደቡብ ሱዳን መንግሥትና አማጽያኑ መካከል በሁለት ሳምንታት ውስጥ የተከናወነ ሁለተኛው ውጊያ ነው ተብሏል፡፡

ምድሪቷ የጦር ምድር ትሁን የተባለች ይመስል በእርስ በርስ ግጭቶች የበርካታ ዜጎችዋን ህይወት እንደ ቀላል እያጣች፣ አዳጊዎቿን ጦር እያስታጠቀች፣ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎቿ ደግሞ ወደ ጎረቤት ሃገራት እየተሰደዱባት ይገኛሉ ደቡብ ሱዳን፡፡

ለአብነት ይጠቀስ ቢባል እንኳን በኡጋንዳ ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሃገሪቱ ስደተኞች ይገኛሉ፡፡ 

ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት የሃገሪቱን ሰላም ለመመለስ ጥረታቸው እንደቀጠለ ቢሆንም  በሃገሪቱ መንግስትና በአማጽያኑ መካከል እርቀ ሰላም መውረድ አልቻለም፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት እንኳን በሃገሪቱ ኒያልዲ በምትባል አካባቢ በተቀሰቀሰ የአንድ ሰዓት ጦርነት ቢያንስ 19 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል ፣በርካቶችም ቆስለዋል፡፡

ይህ በሆነ በሁለት ሳምንት ውስጥ በሃገሪቱ ሰሜን ምስራቅ ክፍል በምትገኘው ዋአት በተባለች አካባቢ በደቡብ ሱዳን መንግስት እና ሪክ ማቻር በሚሩት ታጣቂዎች መካከል በተካሄደ የሶስት ቀናት የጥይት እሩምታ ከሁለቱም ወገን ቢያንስ 100 ሰዎች ተገድለዋል፡፡

የሲጂቲኤን ዘገባ እንደሚያሳየው ከሆነ የሃገሪቱ ጦር ሃይሎች ቃል አቀባይ ብርጋዴል ጀነራል ሉል ሩአይ ኮንግ ውጊያው የተጀመረው ሪክ ማቻር በሚመሩት አማፂያን ቢሆንም አፃፋውን መልሰናል 91 ታጣቂዎችን ገድለናል ብለዋል፡፡

የአማፂያን ቡድኑ ቃል አቀባይ ሜቢዮር ጋሬንግ በበኩላቸው የውግያው መንስኤ መንግስት ነው በማለት ይከሳሉ፡፡ ቡድናቸውም በርካታ የመንግስት ወታደሮችን እንደገደለም ነው የተናገሩት፡፡

‹‹በጦር ሜዳ ላይ አንዱ ወገን መሸነፉ ያለ ነው መንግስትም በቁጥር የበዙ ወታደሮቹን እንደገደልንበት መቀበል አለበት››ም ብለዋል፡፡