ሱዳን ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጧን አስታወቀች

ደቡብ ሱዳን አሜሪካን ከጣለችባት የኢኮኖሚ ማዕቀብ ለመላቀቅ ስትል ግንኙነቷን ማቋረጧን አስታወቀች ፡፡

ሱዳን ከደቡብ ሱዳን ጋር ከተለያየችበት እ.ኤ.አ ከ2011 ወዲህ ኢኮኖሚዋ እንዲያገግም እና ራሷን ለመቻል እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷ እንዲጠናከር ብዙ መሥራቷ ነው  የተገለጸው ፡፡

አሜሪካ እና ሱዳን እ.ኤ.አ በ1967 በተጀመረው የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው በአረብ እስራኤሉ ጦርነት ምክንያት ሱዳን እስክታቋርጥ የተጠናከረ እንደነበር ይነገራል፡፡

ከ5 ዓመት በኋላ መልሶ የተገነባው የሁለቱ አገራት ግንኙነት በተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጥቅሞች የተሳሰረ ነው፡፡ 

ሱዳን እኤአ ከ2011 ወዲህ ከአሜሪካ የምታገኘው ወታደራዊ እና ኢኮኖሚዋን የምትደግፍበት የገንዘብ ድጋፍ አገሪቱ በዋሽንግተን ቁጥጥር ስር እንድትውል አድርጓታል የሚሉም አሉ፡፡

ሱዳን ትሪቡን በዘገባው እንዳመላከተው  ካርቱም አሁን ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድቋርጥ የትራምፕ አስተዳደር ጫና በግልፅ የሚታይ ነው፡፡

ካርቱምና ፒዮንግያንግ ለዓመታት በወታደራዊ እርዳታ፣ ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ እንዲሁም ሁለቱ ሱዳኖች ወደ መለያየቱ ሲያመሩ በነበረው ሂደት የምክረ ሀሳባዊ ድጋፍ ሲለዋወጡ እንደነበር ይነገራል፡፡

እኤአ ከ2011 ወዲህ ሱዳን ፊቷን ወደ አሜሪካ ካዞረች በኋላ ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት ብታጠናክርም አገራቱ ብዙም አልተራራቁም ነው የሚባለው፡፡

ካርቱም ከፒዮንግያንግ ጋር በነበራት ምስጢራዊ ግንኙነት መካከለኛ መጠን የባሊስቲክ ሚሳኤል፣ አነስተኛ መጠን ሚሳኤሎችንና ፀረ ታንክ ሚሳኤሎችን ለመግዛት ተዋውላ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይህን የውል ግንኙነት የሰማችው አሜሪካ ከሱዳን ጋር ያላትን ድጋፍ ተኮር ወዳጅነቷን ማላላት ጀምራለች፡፡ ከዚህም ባለፈ አገሪቱ ለሰብዓዊ መብቶች ቦታ የላትም በሚል አመክንዮ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀቦችን እንደጣለችባት ዊክሊክስ ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡

የፕሬዝደንት ትራምፕ አስተዳደር አገሪቱን በግልፅ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታቋርጥ በተደጋጋሚ አስጠንቅቋት ነበር፡፡

ይህን ተከትሎም ሱዳን ለሰሜን ኮሪያ ቀድሞ የተለሳለሰ ግንኙነቷን በይፋ ማቋረጧን አስታውቃለች፡፡

ካርቱም ለፒዮንግያንግ የላከችውን ይፋዊ የፍቺ ደብዳቤ ለነጩ ቤተመንግስት በግልባጭ መላኳም ነው በሱዳን ትሪቡን ዘገባ ላይ የተገለፀው፡፡

የሱዳን ባለስልጣኖች እንደሚሉት አገራቸው ለአሜሪካ ወዳጅነት ስትል የከፈለችውን መስዋዕትነት ተመልክተው ፕሬዝደንት ትራምፕ የጣሉትን ማዕቀብ ያነሳሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡

አሜሪካ በሱዳን ላሉ የግጭት አካባቢዎች መፍሔን በማበጀት፣ ለዜጎቿ ሰብዓዊ አገልግሎት በመስጠት፣ መሠረት ልማትን በመገንባት፣ አገሪቱን ከሽብር በመታደግ እና  ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንድትሰጣት ሱዳን ትፈልጋለች፡፡

በአንፃሩ ደግሞ አሜሪካም ሱዳን የሀያሏን አገር ትዕዛዝ እንድታከብርና ለሰብዓዊ መብት እና ለዴሚክራሲ እንድትቆም መፈለጓ አይቀርም፡፡ ሱዳንና ሰሜን ኮሪያንም ያለያያቸው ይህ ሳይሆን እንዳልቀረ ነው የተነገረው ሱዳን ትሪቡን እንደዘገበው፡፡