የኡጋንዳ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ፍትሃዊነት እንደሚጎድለው ተመለከተ

በኡጋንዳ የሚሠጠው የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ፍትሃዊነት እንደሚጎድለው ተገልጿል፡፡

ኡጋንዳ እኤአ በ2040 መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሠለፍ የያዘችው እቅድ እንዲሳካ ፍትሃዊ የሆነ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት መዘርጋት አለባት ተብሏል፡፡

ለምጤና ሃብት ችግሩ መንስኤ የተባለው ደግሞ ዜጎች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት አለማግኘታቸውን  ነው  ተብሏል ።

የ39 አመቷ ወይዘሮ ማሪያም ናባታንዚ ገና በለጋነት እድሜዋ ነበር ትዳር የመሠረተችው፡፡ አሁን ላይ 44 ልጆችን ወልዳ በማሳደግ ላይ ነች፡፡ በ13 አመቷ ትዳር የመሠረተችው ናባታንዚ ስለትዳር ሳታውቅ ትዳር መሥርታ በልጅነቷ ልጅ ታቅፋ የቤተሰብ ኃላፊነትን እየተወጣች ትገኛለች፡፡  

ናባታንዚ  ተገቢውን የሆነ መደበኛ ትምህርት አለመማሯ፤በድምሩ ፍትሃዊ የሆነ የጤና ጥበቃ አገልግሎት  አለመኖሩ ነው በተገቢው ሁኔታ  የቤተሰብ  ምጣኔ አገልግሎትን ተጠቃሚ  እንዳትሆን አድርጓታል ፡፡    

ጥቅምት አጋማሽ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስነ ህዝብ ፈንድ ያወጣው ጥናት እንዳመለከተው ፍትሃዊ ያልሆነ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተደራሽ ላይሆን የሚችልበት ምክንያት ሀገራት የሚያመነጩት ሃብት ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ መሆን ሲሳነው ነው፡፡

እድገቱ  ሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለበት ሀገራት ሊዘነጉት እንደማይገባም ጥናቱ ጠቁሟል፡፡  

44 ልጆችን እንደወለደችው ናባታንዚ ባይተዋር መሆን እንደሌለባቸውም ነው ጥናቱ ያመለከተው፡፡  

ባለፈው ዓመት በኡጋንዳ መንግስት የተጠና የሕዝብ ቁጥርና ጤና ዳሰሳ ደግሞ 28 በመቶ የሚሆኑ ኡጋንዳውያን እንስቶች ዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ መጠቀም ቢፈልጉም እድሉን ሊያገኙት አለመቻላቸውን ነው ያስቀመጠው፡፡

ብዙዎቹ ደግሞ ገና በልጅነታቸው ወደትዳር እንዲገቡ የሚገደዱ ናቸው እንደ ጥናቱ፡፡

ይሄው የዳሰሳ ጥናት እንደሚረጋግጠው እድሜያቸው ከ20-24 የሆኑ 49 በመቶ ኡጋንዳዊያን ትዳር የያዙት 18ኛ አመት ልደታቸውን ሳያከብሩ ነው፡፡ ያለእድሜ ጋብቻ ደግሞ ሴቶች ሳይፈልጉና ሥልጠና አካላዊ ቁመና እንዲያረግዙ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል፡፡

በዚሁ የተነሳ ዓለም ላይ በርካታ ወጣት እንስቶች ከሚያረግዙበት ሀገራት ኡጋንዳ ከፊተኞቹ ተጠቃሽ ሆናለች ይላል ዴይሊ ሞኒተር በዘገባው፡፡ 

ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ደግሞ በተለየ ሁኔታ ተባብሶ ከ20-25 በመቶ ወጣት የኡጋንዳ እንስቶች እርጉዝ ናቸው ተብሏል፡፡      

የወጣቶቹ እርግዝና ለህዝብ ቁጥር መጨመር የአንበሳውን ድርሻ እየያዘ ስለመምጣቱም ተነግሯል፡፡

ኡጋንዳ አሁን ዓመታዊ የህዝብ እድገቷ 3 በመቶ ነው፡፡ ይህም ሀገሪቱን በአለም ላይ ፈጣን የህዝብ እድገት ከሚታይባቸው ሃገራት ግንባር ቀደም ተጠቃሽ እንድትሆን አድርጓታል፡፡

ኡጋንዳ ከህዝቧ የሚበዛውን ቁጥር የያዙት ህጻናት መሆናቸው  ብቁ የሰው ሀይል እንዳይኖራት ያሉትም ህጻናትን በማሳደጉ እንዲጠመዱ አድርጓል፡፡

ችግሩ ከዚህ አልፎ የምታመነጨው ሀብት ለድህነት ቅነሳው የሚኖረው ሚና እንዳይጎላ አድርጓል፡፡

በተለይም በቤተሰብ ደረጃ የተሻለና ዘመናዊ አኗኗርን እውን ለማድረግ ዑጋንዳ ማድረግ ያለባት  ፍትሃዊ የሆነ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በሀገሪቱ ሁሉም አከባቢዎች ተግባራዊ ማድረግ ነው ሲሉ የዘርፉ ሙህራን  መክረዋል፡፡

ሴቶች እንዳይማሩ የሚያግዱ እንቅፋቶችን ማስወገድና ከወንዶች እኩል በዓለም አቀፉ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አድሉን መፍጠር ይገባታልም ነው የተባለው፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስነ ህዝብ ፈንድ (UNFPA) ኢ ፍትሃዊነትን ለማስወገድ ኃይሉ እጃችን ላይ ነው ይላል፡፡

ይህ ኃይል ደግሞ ሴቶች ጥራት ያለው የቤሰብ ምጣኔ እንዲያገኝ መሥራት ነው ብሏል፡፡ ኡጋንዳ በ2040  መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች እንዲኖሩኝ እየሰራሁ ነው ብላለች፡፡

እቅዷ ይሳካ ዘንድ የቤሰብ ምጣኔ አገልግሎት ላይ መስራት እንደሚገባትና ለእድገት ቁልፍ ስለመሆኑም ምክረ ሀሳብ ቀርቦላታል ዴይሊ ሞኒተር እንደዘገበው፡፡