አይ ኤስ ከሶሪያ ምድር ሊጠፋ እንደሚችል አስተያየት ሠጪዎች አመለከቱ

አይኤስ ከሶሪያ  ምድር እየተዳከ መጥቶ በቅርቡ ሊጠፋየሚችልበት ሁኔታ እንዳለ አስተያያት  ሠጪዎች  አመለከቱ ።

አይ ኤስ አሁን ላይ ተቆጣጥሯቸው የነበሩትን በርካታ ይዞታዎች እየተነጠቀና እየተዳከመ መምጣቱን ተከትሎ በቅርብ ጊዚያት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ከሶሪያ ምድር ሊጠፋ እንደሚችል አስተያየቶች እየተሰጡ ይገኛል፡፡

ከሳምንታት በፊት የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይል ከአሜሪካ ባገኘው ድጋፍ በመታገዝ ከአራት ወራት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ የአሸባሪው ቡድን ዋና መቀመጫ ሆና ስታገለግል የነበረችውን የራቃ ግዛትን በማስለቀቅ በእጁ ማስገባቱ ይታወሳል፡፡

አሸባሪው ቡድን የራቃ ግዛትን ጨምሮ ሌሎች በሶሪያ ተቆጣጥሯቸው የነበሩ ግዛቶችን ሳይወድ በግድ እንዲለቅ መደረጉና አሁን ደግሞ በሶሪያ ሰፊውን የነዳጅ ክምችት ይዛ የምትገኘውን የአል ኦማር ግዛትን መነጠቁ በእርግጥም አሸባሪው አይ ኤስ በሶሪያ ምድር ክስረት እንደገጠመው ማሳያ ነው የሚሉም በርካታ  አስተያያት ሠጪዎች አሉ ፡፡

የኩርዳዊያንና የአረብ ኃይል ታጣቂዎች በብዛት የሚገኙበት የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ሀይል አሁን ለአሸባሪው አይ ኤስ ፈተና ሆነዋል፡፡

ከአሜሪካና ከእነዚህ ሀይሎች የሚሰነዘረውን ጥቃት መቋቋም የተሳነው የሽብር ቡድኑ ኢኮኖሚያዊ አቅሙን የሚያዳብርባትን እና የሚተማመንባትን የአል ኦማር ግዛትን ማጣቱ ምናልባትም ተመልሶ እንዳያንሰራራ ያደረገዋልም እየተባለ ነው፡፡

የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይል ቃል አቀባይ ላኢላ አል አብዱላህ ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አይ ኤስ የአል ኦማር ግዛትን ለብዙ ወራት ተቆጣጥሯት የቆየ ሲሆን ከአሜሪካ ድጋፍ የሚደረግለት ኃይላችን ባደረገው የፀረ ሽብር ዘመቻ በነዳጅ ሀብት የታደለችውን የአል ኦማር ግዛትን በሰአታት ውስጥ ከሽብር ቡድኑ ነፃ ማውጣት ችለናል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የአል ኦማር ግዛት በኢራቅና በሶሪያ ድንበር ላይ በሚገኘው የኤፍራጠስ ወንዝ ምስራቃዊ ክፍል የምትገኝ ከተማ ስትሆን በኢራቅ ከዴር አዝዞር ግዛት ጋር ትዋሰናለች፡፡ ለሶሪያው ፕሬዚዳንት በሽር አላሳድ ታማኝ የሆኑ ሀይሎች ደግሞ በዚህ ሳምንት ወደዚች ቦታ በመግባት የነዳጅ ቦታውን ለመቆጣጠር ከሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ሀይሎች ጦር ጋር ተፋጠዋል፡፡

ከሩሲያ ድጋፍ የሚደረግለት የበሽር አላሳድ ታማኝ ሀይሎችም በሶሪያና በኢራቅ ድንበር በምትገኘው የአል ኦማር ክፋይ የሆነችውን የዴር አዞር የነዳጅ ቦታ ለመቆጣጠር ከሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር ሩጫ ተያይዘዋል፡፡

በሶሪያ የሚገኘው የሰብአዊ መብት ታዛቢ ቡድን እንደገለፀው የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች በነዳጅ ሀብታም ወደ ተባለችው ቦታ በቀላሉ በመግባት መቆጣጠር ችሏል፡፡

ታዛቢ ቡድኑ ከአልጀዚራ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ሀይሎች ወደ አል ኦማር የደረሱት የበሽር አላሳድ ሀይሎች ከነዳጅ ቦታው በአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎች እንዲሸሹ ከተደረጉ በኋላ ነው ብሏል፡፡

የአልጀዚራው ሪፖርተር ሀሽም አህልባራ ከቦታው ሆኖ እንደዘገበው የሶሪያ    ዲሞክራሲያዊ ሀይሎች የአል ኦማር ከተማን ተቆጣጠሩ ማለት እምቅ የሆነ የፋይናንስ አቅም እንዲኖራቸውና ግዛታቸውን እንዲያስፋፉ ይረዳቸዋል ሲል ተደምጧል፡፡

አሁን በሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ሀይል ታጣቂዎች አዕምሮ ዘንድ የሽብር ቡድኑን አግዝፎ ከማየት ይልቅ  የሽብር ቡድኑን ቀሪ ይዞታዎች እንዴት እናስለቅቅና አይ ኤስን ከሶሪያ ምድር እንዴት ሙሉ በሙሉ እናጥፋ የሚል ሆኗል፡፡

አሜሪካ ለሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይል የምታደርገው የፀረ ሽብር ድጋፍ አሸባሪው አይ ኤስን በርካታ ይዞታዎቹን እያሳጣው መምጣቱ በሶሪያ ምድር የሽብር ቡድኑ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ሊጠፋ እንደሚችል ግን የበርካቶች አስተያየት ሆኗል፡፡