የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኡሁሩ ኬንያታን ፕሬዝዳንትነት አፅድቋል

የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኡሁሩ ኬንያታ ፕሬዚደንትነትን አፀደቀ ።  

ራይላ ኦዲንጋ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ መግለጫ በኋላ ኬንያ አለም አቀፍ ፖለቲካዊ  ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡

በኬንያ በዘንድሮ ዓመት ሁለት ጊዜ በተካሄዱት አወዛጋቢ ምርጫዎች በፕሬዝዳንትነት የሚመሯት የኡሁሩ ኬንያታ አሸናፊ መሆናቸው  የቻሉ ሲሆን  ተነቃቃኛቸው ራይላ ኦዲንጋ ግን  ውጤቱን  በፀጋ ለመቀበል አልቻሉም ።   

ፕሬዝዳንት ኡሁሩ በፍርድ ቤት ትእዛዝ አማካኝነት ነሃሴ ወር ላይ ተካሂዶ የነበረውን የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውድቅ በማድረግ ድጋሚ  እንዲካሄድ ባዘዘው መሠረት ኡሁሩ ዋነኛ ተቀናቃኛቸው ራይላ ኦዲንጋ ባልተሳተፉበት ምርጫ 98 በመቶ ድምፅ በማግኘት አሸናፊ ሆነዋል፡፡

የሃገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰኞ እለት ሲመክር ውሎ የኡሁሩን ፕሬዝዳንትነት በይፋ አፅድቆታል፡፡ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታም  ህዳር 19 ላይ ቃለ መሃላ ፈፅመው መንበረ ስልጣናቸውን ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ምክንያት ግጭት ውስጥ የገባችው ኬንያ በሃገሪቱ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ምርጫው ዳግም እንዲካሄድ ተወስኖ ምርጫው በድጋሚ ቢካሄድም አሁንም ግን በሃገሪቱ መረጋጋት አይታይም፡፡

በዳግም ምርጫው ላይ ራሳቸውን ያገለሉት የኬንያ ዋነኛ ተፎካካሪ ፓርቲ ናሳ መሪ የሆኑትን ራይላ ኦዲንጋን የሚደግፉ ዜጎች ኡሁሩ ኬንያታን በመቃወም አደባባይ ላይ  መውጣታቸው ይታወሳል ።

ተቃዋሚዎቹ በተለይም በአንድ ሌሊት የተገደሉባቸውን ሰዎች ለምን ይገደላሉ በማለት እሁድ ላይ እንደወጡ ነው የሮይተርስ ዘገባ የሚያሳየው፡፡       

የሃገሪቱ ፖሊስም ኃይለሥላሴ ተብሎ በተሰየመው አደባባይ ላይ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የነበሩ ዜጎቹን ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ እና የጥይት ተኩስ መፈፀሙን ሲቲዝን ቲቪ ኬንያ የተባለው ቴሌቪዥን ጣቢያ በወቅቱ ዘግቧል፡፡  

የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ እንደሚያሳየው ደግሞ ከውጭ ሃገር ቆይታቸው የተመለሱት የተፎካካሪ ፓርቲው መሪ ኦዲንጋን ለመቀበል በመዲናዋ ናይሮቢ የወጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ኬንያውያንን የሃገሪቱ ፖሊስ በትኗቸዋል፡፡    

የሰብዓዊ መብት ቡድን ከምርጫው ጋር ተያይዞ 50 የሚደርሱ ዜጎች የሞቱ እንደሆኑ እና አብዛኞቹ በፖሊስ የተገደሉ  መሆናቸውን ፕሬስ ቴሌቪዥን በዘገባው ጠቁሟል፡፡

የተፎካካሪ ፓርቲው መሪ የሆኑት ባለ ሃብቱ ራይላ ኦዲንጋ እሳቸው ከውጭ ሃገር ቆይታቸው ከተመለሱበት ከዓርብ ጀምሮ ቢያንስ 31 ሰዎች እንደተገደሉ በመጥቀስ በኬንያ አስቸኳይ የዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ኦዲንጋ አክለውም ‹‹ጥቃቱ በመንግስት የተደገፈ የጭካኔ ተግባር ነው አስቸኳይ እርዳታ እንፈልጋለን፡፡›› ብለዋል፡፡