ሮበርት ሙጋቤ ያለመከሰስ ዋስትና ተሰጣቸው

የቀድሞው የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ እና ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ ያለመከሰስ ዋስትና እንደተሰጣቸው የሀገሪቱ ወታደራዊ ሃይል ዛሬ አስታወቀ።

የቀድሞው የነጻነት ታጋይና አገሪቱን ለ37 ዓመታት የመሩት ሮበርት ሙጋቤ በቅርቡ በራሳቸው ፈቃድ ስልጣናቸውን መልቀቃቸው ይታወሳል።

ሮበርት ሙጋቤ የሀገሪቱ የፓርላማ አባላት ፕሬዚዳንቱን በመክሰስ ከስልጣን ለማንሳት ውይይት በጀመሩበት ሰዓት ነበር ከስልጣናቸው መልቀቃቸውን ይፋ ያደረጉት።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት በፈፀሙባቸው ስህተቶች እንደሚከሰሱ ወታደራዊ ሀይሉ ሲገልፅ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ የሀገሪቱ ወታደራዊ ሃይል የቀድሞው የዚምባብዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ እና ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ ያለመከሰስ ዋስትና እንደተሰጣቸው አስታውቋል።

የዚምባብዌ የመከላከያ ሰራዊት ቃል አቀባይ ኮለኔል ኦቨርሶን ሙግዊሲ እንደተናገሩት፥ ለቀድሞው መሪ እና ባለቤታቸው የደህንነት ጥበቃ እና ዋስትን እንዲደረግላቸው ስምምነት ተደርሷል።

ባልና ሚስት በአገሪቱ ውስጥ እንዲቆዩም ተፈቅዶላቸዋል ነው የተባለው (ኤፍ ቢ ሲ )።