በግብጽ በደረሱ ሁለት ጥቃቶች አስራ ሁለት ሰዎች ተገደሉ

በግብጽ በደረሱ ሁለት ጥቃቶች አንድ የሀገሪቱን የፖሊስ መኮንን ጨምሮ 12 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ፡፡

በሰሜን ሲናይ አንድ የፖሊስ መኮንንና  5 ወታደሮች መኪናቸው ውስጥ እያሉ የተጠመደባቸው ቦንብ ፈንድቶ ሲሞቱ በተመሳሳይም ኤል አሪሽ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ባንክ ውስጥ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ሁለት ሰዎች መገደላቸውም ነው የተነገረው፡፡

በኤል አሪሽ ከተማ ታጣቂዎች በተኮሱት ሮኬት ባንኩን ሲጠብቅ የነበረ አንድ የፖሊስ አባል መግደላቸውን ተከትሎም በስፍራው የነበሩ ፖሊሶች ተኩስ ቢከፍቱም ታጣቂዎቹ ወዲያውኑ ከቦታው መሸሻቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል፡፡

የግብጽ የአገር ውስጥ  ጉዳይ ሚኒስተር በቦታው ተገኝተው ስለሁኔታው ለመናገር ብዙ ጊዜ ስለመውሰዳቸው እማኞቹ አክለው አስታውቀዋል፡፡

አሸባሪዎች በሰሜን ሲናይ ባጠመዱት ቦንብ ደግሞ አንድ የፖሊስ መኮንንና 5 ወታደሮች መኪናቸው ውስጥ እያሉ መገደላቸውን የግብጹ የጦር ኃይል አስታውቋል፡፡

ወታደሮቹ ጥቃት የተፈጸመባቸው በታጣቂዎቹ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ለመፈጸም በተንቀሳቀሱበት ሰዓት መሆኑም ተመልክቷል፡፡ 
የቦንብ ጥቃቱ ትክክለኛ ቦታ ያልተገለጸ ሲሆን የጦር ኃይሉ በተለያየ ጊዜ ባደረገው ድንገተኛ የማጥቃት ዘመቻ 3 ታጣቂዎች መገደላቸውም ተጠቅሷል፡፡
የፀጥታ ኃይሎች በሰሜን ሲናይ ለበርካታ አመታት ዳይሽ ከተሰኘው ታጣቂ ቡድን ጋር ሲዋጉ ነበር፡፡ በውጊያውም በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች እና ፖሊሶች ተገድለዋል፡፡
አሁን አሁን ደግሞ ጥቃቶች ኢላማቸውን ሰላማዊ በሆኑ ሙስሊሞችና እና ክርስቲያኖች ላይ እያደረጉ መምጣታቸው በስፋት ስለመስተዋሉም ብዙዎች የሚስማሙበት ጉዳይ ነው፡፡
ባለፈው ወር በግብጹ አል ራዋዳ አንድ መስጊድ ላይ በደረሰ አሰቃቂ ጥቃት ከ 300 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል፡፡   
የግብጹ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ ኤልሲሲም የመስጊድ ጥቃቱን ተከትሎ ወታደሮቻቸውን በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ የታጣቂ ቡድኑን እንዲደመስሱ ማዘዛቸው አይዘነጋም፡፡ 
(ምንጭ:ቲአርቲ ዎርልድ )