ሱዳን በግብጽ የሚገኙትን አምባሳደሯን መጥራቷ ተገለጸ

ሱዳን በግብፅ የሚገኙትን አምባሳደሯን ለውይይት መጥራቷ ተገለፀ፡፡

ሮይተርስ ከሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አገኘሁት ባለው መረጃ መሠረት በካይሮ የነበሩት የሱዳኑ አምባሳደር ለምክክር ወደ ሀገራቸው ተጠርተው ተመልሰዋል፡፡

ግብፅ በበኩሏ ተመጣጣኝ ምላሽ ለመሥጠት ሁኔታውን እያጤነች እንደምትገኝ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መሥሪያ ቤቷ በኩል ገልፃለች፡፡

በግብፅ እና በሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት በሁለቱ ሀገራት ድንበር በሚገኘው እና ሀላያብ ትሪያንግል በተባለው ስፍራ የይገባኛል ጥያቄ እንዲሁም በአባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም ላይ ባላቸው ልዩነት ምክንያት ውጥረት ውስጥ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ካሁን በፊት ግብፅ በሱዳን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ትገባለች በሚል ክስ የምታቀርበው ሱዳን የግብፅ የግብርና ምርቶች ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ ማገዷን ይታወሳል ብሏል ዘገባው፡፡