የመንግሥታቱ ድርጅት 110 ሺህ ሶማሊያውያን ስደተኞች ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አስታወቀ

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ 110 ሺህ የሚጠጉ የሶማሊያ ስደተኞች በሶስት አመታት ውስጥ ከተለያዩ ሀገራት ወደ አገራቸው ተመልሰው መላካቸውን አስታወቀ ፡፡

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ተቋም ሀሙስ እለት እንዳስታወቀው እኤአ ከ2014 ወዲህ ከ100 ሺህ በላይ ሶማሊያዊ ስደተኞችን ይኖሩበት ከነበረበት 6 ሀገራት በፍቃደኝነት ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 75 ሺህ የሚጠጉት ስደተኞች ከኬንያ የተመለሱ ሲሆን፥ 30 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ከየመን ወደ ሶማሊያ መግባታቸው ነው የተነገረው፡፡

ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው የመመለሱን ሂደት የኬንያ አየር መንገድና የየመን ባህር ሀይል እንዳገዙት ተጠቁሟል፡፡

ጂቡቲ፤ኤርትራ አና ቱኒዚያ በጥገኝነት ይኖሩ የነበሩ የሱማሊያ ስደተኞች ከሚገኙባቸው ሀገራት ውስጥ ተጠቃሽ መሆናቸውም ነው የተመላከተው፡፡

በሶማሊያ የፖለቲካ እና የደህንነት ሁኔታ እየተረጋጋ መምጣት እና የሱማሊያ ስደተኞችን የሚቀበሉ ሀገራት ግፊት  ለሶማሊያ ስደተኞች ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ ለሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ  እንዳደረገ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

ይሁንና ከኬንያ ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ሂደት  በዝናብ ሳቢያ የአየር ጉዞው  በመቋረጡና በሱማሊያ አሁን ባለው አለመረጋጋት ምክንያት ለጊዜው መቋረጡም ነው የተመለከተው፡፡

ለሶስት አስርት አመታት በዘለቀው የሱማሊያ እርስ በርስ ግጭት ከ2 ሚሊዬን በላይ ሰዎች ወደተለያዩ ቦታዎች መፈናቀላቸው ድርጅቱ ገልጾ 1 ሚሊዬን የሚሆኑቱ አዛው አገራቸው ውስጥ በተለያየ ቦታ ላይ ስለመስፈራቸው የዥንዋ ዘገባ ያሳያል፡፡

በተመሳሳይ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሰሜናዊ ምስራቅ የአፍሪካ ቀንድ በምትገኘው ሶል ግዛት በሚኖሩ የፑንት ላንድና ሶማሌ ላንድ የደህንነት ሃይሎች መካከል የተከሰቱ ግጭቶች ተከትሎ፥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መልዕክተኛ ሶማሌላንድና ጎረቤቷ ፑንትላንድ የደህንነት ኃይሎች እርስ በእርስ የሚያደርጉትን ግጭት ትተው ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሶማሊያ መልዕክተኛ ሚካኤል ኬቲንግ በሱማሌላንድ ዋና ከተማ ሀርጌሳ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የእኛ ድርሻ በቀጠናው ያለውን ውጥረት ለመቀነስ ይረዳ ዘንድ ሁለቱም ወገኖች በፍጥነት ወደ ክብ ጠረጴዛ መጥተው ያለባቸውን አለመግባባት እንዲፈቱ ነው፤ችግሮቻቸውን ለመፍታት ግን ጦርነትን አማራጭ ካደረጉ ተሳስተዋል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡( ምንጭ: የዠንዋ)