ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በእንግሊዝ የሚያደርጉትን ይፋዊ ጉብኝት ሠረዙ

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ እንግሊዝ የሚያደርጉትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት መሰረዛቸውን አረጋገጡ፡፡

ፕሬዚደንቱ ወደ ለንደን ያቀኑ የነበረው ከይፋዊ የሥራ ጉብኝት በተጨማሪ አዲሱን የአሜሪካ ኤምባሲ ጽህፈት ቤት ለመመረቅ እንደነበርም ታውቋል፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ የለንደን ጉዟቸውን የሠረዙት እንግሊዛውያን በአሜሪካ ላይ እያሰሙ ያለው ተቃውሞ ማየሉን ተከትሎ ነው፡፡ 

አሜሪካ ከ58ዓመት በፊት እ.ኤ.አ በ1960 በእንግሊዝ መልዕክተኛዋን ስታስቀምጥ የከፈተችው ኤምባሲ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በምዕራብ አውሮፓ ከተከፈቱ የአገሪቱ ኤምባሲዎች ግዙፉ እንደነበር ይነገራል፡፡

በ1960 የተጀመረው የሁለቱ አገራት የተጠናከረ ወዳጅነት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ  ቢያስቆጥርም በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ሥልጣን ዘመን ግንኙነታቸው ወደ ማሽቆልቆል እንዳመራም  ተገልጿል፡፡

ሁለቱ አገራት አሁንም በሁለትዮሽ ትስስራቸው በአውሮፓ እና አሜሪካ መካከል ዘላቂ የፖለቲካ ኢኮኖሚ እንዲጎለብት የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

ዋሽንግተን ከለንደን ጋር ያላትን ትብብር ለማጠናከር ከ1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገንዘብ የፈጀ ኤምባሲ በመገንባት ቀድሞ ከነበረበት ዌስት ሚኒስቴር ግሮስ ቬነር አካባቢ ወደ ናይን ኤልምስ ከተማ አዘዋውራለች፡፡ 

ኤምባሲው በኳታር የስነ ህንፃ ባለሙያዎች የተገነባ ሲሆን፤ የዘመኑን የህንፃ ኪነ ጥበብ የተላበሰ እንደሆነም  ተመልክቷል ፡፡ የህንፃው ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ገፅታው የወጣለትን ገንዘብ የሚመጥን  መሆኑን ብዙዎች  ይስማሙለታል። 

 በዓለም በኤምባሲ ደረጃ ውድ የተባለውን ተቋም በእንግሊዙ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ይመርቃሉ የተባሉት ፕሬዚደንት ትራምፕ ጉዟቸውን ሰርዘው በምትካቸው የውጭ ጉዳያቸውን ሬክስ ቴለርሰንን እንደሚልኳቸውም ታውቋል፡፡

ትራምፕ ጉዟቸውን የሰረዙት ከቀድሞው ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ የሥልጣን ዘመን ጀምሮ እንግሊዛውያን በአሜሪካ ላይ ያሰሙት የነበረው ተቃውሞ አሁን የትራምፕን የመምጣት ወሬን ተከትሎ በማየሉ ነው ፕሬዚደንቱ ወደ ለንደን እንደማይጓዙ የገለፁት፡፡

ፕሬዚደንት ትራምፕ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ እኔ የኦባማ የሥልጣን ዘመን ተከታይ አይደለሁም፡፡ በእርሱ ጊዜ በተፈፀመ ስህተት እና በእርሱ ጥፋት አልጠየቅም ሲሉ መቅረታቸውን ነው የገለፁት፡፡ ፕሬዚደንቱ ተቃውሞውን በመፍራት ጉዟቸውን ሰርዘዋል ሲሉ የዘገቡ የመገናኛ ብዙሃንም ተደምጠዋል፡፡ 

ፕሬዚደንቱ የእንግሊዝን እና አሜሪካን የሁለትዮሽ ግንኙነት የሚያጠናክር ይፋዊ የሥራ ጉብኝታቸውን መቼ እንደሚያደርጉ አልተጠቀሰም፡፡ 

የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቴሬሳ ሜይ ፕሬዚደንት ትራምፕ ምርጫውን አሸንፈው በበዓለ ሲመታቸው ከተገኙ ቀዳሚ የአውሮፓ አገራት መሪዎች አንዷ እንደሆኑም ይታወሳል ።( ምንጭ: ዘ ኢንዲፔንደንት )