ኢጋድ የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነትን የጣሱ አካላትና የሰላም ስምምነቱ የተጣሰባቸውን አካባቢዎች ይፋ አደረገ

የኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የደቡብ ሱዳን የተኩስ ማቆምና የጠብ ጠብ አጫሪነት ስምምነት መጣስን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል። ምክር ቤቱ የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት መጣስ እንዳሳሰበውም አስታውቋል።

ምክር ቤቱ በተኩስ ማቆምና የሽግግር የፀጥታ አወቃቀር ግምገማ ቡድን አማካኝነት በደቡብ ሱዳን በታህሳስ 2010 ዓ.ም የተፈረመውን የተኩስ ማቆምና ለሲቪሎች ከለላ የመስጠቱን ስምምነት በሚጣረስ መልኩ የፆታዊ ጥቃትና የህጻናት ወታደሮች ምልመላ መካሄዱን የሚገልፅ ሪፖርት እንደደረሰው አስታውቋል።

በዚህም በንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ፣ የከፋ አእምሯዊና አካላዊ ጉዳት፣ አስገድዶ መድፈር፣ ጾታዊ ጥቃትና ዝርፊያ መፈጸሙን ምክር ቤቱ አመልክቷል።

የሰላም ስምምነቱ የተጣሰው በመንግስትና በሌሎች ተቀናቃኝ ሃይሎች መሆኑን ያስታወቀው ሪፖርቱ ይህም ጾታን መሰረት ያደረገ ጥቃትን ያካትታል።

የደቡብ ሱዳን መንግስትና ሌሎች ኃይሎች ይህን መሰል ወንጀል የፈጸሙ አካላትን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አጣርተው ለህግ እንዲያቀርቡና ሪፖርት እንዲያደርጉ ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

በአገሪቱ አሁን ድረስ ህጻናትን ለውትድርና የመጠቀሙ ሂደት መቀጠሉን በተኩስ ማቆምና የሽግግር የፀጥታ አወቃቀር ግምገማ ቡድን ሪፖርት አረጋግጧል። ይህም በእጅጉ እንዳሳሰበው ምክር ቤቱ ያስታወቀው።

ሁሉም የደቡብ ሱዳን ሃይሎች ከጠብ አጫሪነት በመታቀብ ለሰላም ስምምነቱ መተግበር ገንቢ ሚና እንዲጫወቱም ምክር ቤቱ ጠይቋል።

አለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ለሰላም ስምምነቱ ትግበራና ለግምገማ ቡድኑ ድጋፉን እንዲያጠናክር የጠየቀው ምክር ቤቱ፤ ስምምነቱን በጣሱ አካላት ላይ ተመጣጣኝ እርምጃ እንደሚወስድ ባወጣው መግለጫው አስታውቋል፡፡ምንጭ- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር