የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ተቋማት ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ቁርጠኛ መሆን እንዳላባቸው ተመለከተ

የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ተቋማት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምለማምጣትቁርጠኛ መሆን እንዳለባቸው  ተመለከተ ፡፡

የሀገሪቱ ተፋላሚ ኃይሎች የፈረሙትን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚያስችል ፎረም በኢጋድ አማካኝነት ለሁለተኛ ጊዜ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡  

በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየተካሄደ ባለው ጥረት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ  ከቃል በዘለለ በቁርጠኝነት እና በተግባር የተደገፈ ሥራን ማከናወን እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡

አመታትን ያስቆጠረው የደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ግጭት በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስት አደራዳሪነት ተፋላሚ ኃይሎችን ለማስማማት እና ለሀገሪቷ ህዝቦች ሰላምን ለማምጣት የሚያስችል ጉባኤ በአዲስ አበባ ሲካሄድ  ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡

ባሳለፍነው ወር የሀገሪቱ ተፋላሚ ኃይሎች በአዲስ አበባ ተገናኝተው የተኩስ አቁም ስምምነት ማደርጋቸው የሚታወስ ነው፡፡ 

ይህንን ስምምነት ተከትሎ የተለያዩ የዓለም ሀገራትና ድርጅቶች ኃይሎች የገቡትን ቃል ማክበር እንዳለባቸው ሲያሳስቡም ሲያስጠነቅቁም ቆይተዋል፡፡

ከሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባ በመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን  የመስብሰቢያ አዳራሽ ዳግም የሰላም ስምምነቱ በዘላቂነት ተግባራዊ በሚደረግበት ጉዳይ ለመምከር ሁሉም አካላትን ያሳተፈ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በዚህ ጉባኤ ላይ በሀገሪቷ ውስጥ ለአመታት በተካሄደው የእርስ በርስ ግጭቱ እንዲያበቃና በሀገሪቱ ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ በውይይቱ ላይ የሚሳተፉ ኃይሎች ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የወቅቱ የኢጋድ አባል ሀገራት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ  ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አሳስበዋል፡፡

የሀገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች ባለመስማማታቸው ህዝቡ እየተሰቃየ መሆኑን ያስረዱት ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ለዚህ ደግሞ ፓርቲዎቹ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናገርዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከዚህ ቀደም ስምምነት ለማድረግ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል ያሉት ዶክተር ወርቅነህ፡፡ይህም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

እነዚህን አካላት ለማስማማት እየተደረገ ያለው የአሁኑ ጥርት ግን ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ የመጨረሻው እድል እና ሊጠቀሙበት የሚገባ መሆኑን ነው በንግግራቸው ያሳሰቡት፡፡

የሰላም አየር የናፈቃቸው የደቡብ ሱዳን ህዝቦች  የሚፈልጉትን ሰላም እና ብልፅግና ለማምጣት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የትኛውንም አይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ነው የተገለፀው፡፡

አሁን የተለያየ አመለካከት ይዘው ለየቅል ያሉት የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ስምምነቱ እንዲመጡ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየሳሳበም ይገኛል፡፡( ምንጭ:የሱዳን ትሪቡን )