ሱዳን የዶሃ መግባቢያ ሰነድ ላይ ማሻሻያ የማትፈልግ መሆኗን አስታወቀች

የሱዳን ባለስልጣናት ሱዳን የዶሃው የመግባቢያ ሰነድ ላይ ምንም አይነት ማሻሻያ እንዲደረግበት እንደማትፈልግ አስታወቁ ።

የዳርፉር ሰላም አስከባሪ ጽህፈት ቤት ሊቀመንበር ማግዲ ካህላፍ አላህ እንደተናገሩት በዳርፉር ሰላምን ለማምጣት ታስቦ ከዚህ ቀደም የፀደቀው የዶሃው የመግባቢያ ሰነድ ከማንኛውም የአማጺያን ቡድን ጋር ከስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል የመጨረሻው መንገድ ሆኖ ይቀጥላል፡፡

ከሱዳን መንግስት የተውጣጡ ልኡካን በአንድ በኩል የፍትህ እና እኩልነት ንቅናቄ ቡድን እንዲሁም የሱዳን ነጻነት ንቅናቄ ወይም ሚኒ ሚናዊ የተውጣጡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በሌላ ወገን ከሳምንት በፊት  በበርሊን ውስጥ ባካሄዱት የሁለት ቀናት ስብሰባ በምዕራባዊ ሱዳን ክልል ያለው ግጭት መቋጫ ያገኝ ዘንድ የሚደረገው ድርድር ከመጀመሩ በፊት ለመግባባት በሚችሉበት የመግባቢያ አዋጅ ላይ ተነጋግረዋል ነው የተባለው፡፡  

ሆኖም ግን አደራዳሪዎቹ እና አስተባባሪዎቹ በአገሪቱ መንግስት እና በታጣቂ ቡድኖች መካከል እኤአ ከሐምሌ 14 2011 የተፈረመውን የዶሃውን የመግባቢያ ሰነድ(ዲዲፒዲ) ማሻሻያ እንዲደረግበት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ስብሰባው ያለ ምንም አመርቂ ውጤት ስለመጠናቀቁ ተመላክቷል፡፡ 

 
የፍትህ እና እኩልነት ንቅናቄ ቡድን ጄኢኤም ቡድን መሪ ጅብሪል ኢብራሂም ለሱዳን ትሪቡን እንደተናገረው ቅድመ ድርድር ስምምነቱ ካርቱም በዶሃው የመግባቢያ ሰነድ ላይ ከሠፈረው ውጭ ምንም ማሻሻያ አልቀበልም በማለቷ ሳቢያ ሊሳካ እንዳልቻለ የገለጸው በቁጭት ነው፡፡ 

ከሱዳኑ የዜና ወኪል ሱና ጋር ቆይታ ያደረጉት ካህላፍ አላህ በበኩላቸው የበርሊኑ ውይይት የተሳካ አልነበረም የሚባለውን እንደማይቀበሉ በመግለጽ ነገር ግን አማጺ ቡድኖቹ የመግባቢያ ሰነዶቹ ላይ ስምምነት ላይ ከመድረሳቸው በፊት የመግባቢያ አጀንዳዎቹን እንዲሻሻሉ መጠየቃቸው ተቀባይነት እንደሌለው ነው የተናገሩት፡፡  

ካህላፍ አክለውም ከአማፅያን ቡድኖች ጋር ወደፊት የሚደረገው ስምምነት ከዶሃ ው የመግባቢያ ሰነድ ጋር አብሮ እንደ ፕሮቶኮል ስምምነት እንደሚካተትም ነው ያስታወቁት፡፡ 

 
የጀርመን፤ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ዩናይትድ ኪንግደም እና ኖርዌይ በቅርቡ ባወጡት ውስጥ የጋራ መግለጫ የሱዳን ፓርቲዎች ለሂደቱ ቁርጠኛ እንዲሆኑ በማበረታታት በሁለቱም ወገኞች እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን አድንቀዋል፡፡

 
የፍትህ እና እኩልነት ንቅናቄ ቡድን እንዲሁም የሱዳን ነጻነት ንቅናቄ ቡድንን ጨምሮ የ2011 የዶሃውን የመግባቢያ ሰነድ ያልፈረሙ ቡድኖች የመግባቢያ ሰነዱ ማዕቀፉ ለውይይት ክፍት እንዲሆን ጥሪ ስለማቅረባቸው ተመልክቷል፡፡ 

 
በሌላ በኩል በአብዱል ዋሂድ የሚመራው እንደ ሱዳን ነጻነት ንቅናቄ ያሉ ሌሎች ቡድኖች ሂደቱን እንደማይቀላቀሉ እና የሚያመጣውን ውጤት እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል ነው የተባለው፡፡

በቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ የሚመራው የአፍሪካ ህብረት ሥራ አስፈፃሚ ፓናል በሀገሪቱ የተሰራፋውን የጦር ግጭቶችን ለማቆም እና በሱዳን የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ሁሉን አቀፍ አማራጭ ሀሳብ አቅርቧል፡፡

እኤአ ከ2015-2016 ውስጥ በመንግስት እና በፍትህ እና እኩልነት ንቅናቄ ቡድን እንዲሁም የሱዳን ነጻነት ንቅናቄ የተቃዋሚ ቡድኖችን በማሰባሰብና በመንግስትና በቡድኖቹ መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ ዓለም አቀፍ ጥረቶች ቢደረጉም ተጨባጭ ውጤቶችን ማግኘት እንዳልተቻለ ተጠቁሟል፡፡

 
የሱዳን ሠራዊት እኤአ ከ 2003 ጀምሮ በዳርፉር የሚገኙ ታጣቂዎችን ሲዋጋ ቆይቷል፡፡

 
የተባበሩት መንግስታት ያስቀመጠው ግምት በግጭቱ ከ 300 ሺ በላይ ሰዎች እንደተገደሉ እና ከ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ትተው እንደተፈናቀሉ ያሳያል ሲል ሱዳን ትሪቡን በዘገባው አስፍሯል፡፡