አሜሪካ በአልሻባብ ላይ በሰነዘረችው ጥቃት 60 የቡድኑ ተዋጊዎች መሞታቸው ተገለጸ

አሜሪካ በፅንፈኛው አልሻባብ ላይ በሰነዘረችው የአየር ጥቃት 60 የቡድኑ ተዋጊዎች መሞታቸው ተገለጸ፡፡

አሜሪካ ጥቃቱን የፈፀመቸው ሶማሊያዊያን አልሻባብ በሞቃዲሾ 500 ንፁኃንን ህይወት የጠፋበትን አንደኛ አመት እያሰቡ ባሉበት ወቅት መሆኑ ታውቋል፡፡ ሆኖም ግን አሜሪካ ከእለቱ ጋር ተያያዥነት እንደሌለው አስታውቃለች፡፡

ሶማሊያዊያን ፅንፈኛው አልሻባብ ቡድን በሞቃዲሾ ባደረሰው የቦንብ ጥቃት ከ500 በላይ ንጹሐንን ህይወት ያጡበትን አንደኛ አመት መታሰቢያ አክብረዋል፡፡

እለቱ ባለፈው አሁድ ታስቦ የዋለ ሲሆን ምንም እንኳን ዘገየ ቢባልም አሜሪካ በአየር ላይ በወሰደችው የአየር ጥቃት 60 የአልሻባብ ተዋጊዎች መገደላቸው ምላሽ ለመሥጠት ዓላማ በማድረግ ነው የሚሉ ሀሳቦች ከሶማሊያውን ዘንድ ተሰምቷል፡፡

የአሜሪካ ወታደሮች ባለፈው ህዳር ወር ባደረሱት የአየር ጥቃት 100 የአልቃይዳ ክንፍ የሆነው አልሻባብ ተዋጊዎች ከሞቱበት ቀጥሎ ይህ ከፍተኛው መሆኑ ተነግሯል፡፡

የዋሺንግተን ወታደር ሀይሎች ከስፍራው እንዳስታወቁትም እርምጃው የከአንድ አመቱ በፊት ጥቃት ቀጥሎ በአልሻባብ ላይ የተወሰደ ከባድ እርምጃ ነው ብለውታል፡፡

እርምጃው የተወሰደው ከባለፈው አርብ አንስቶ ቡድኑ በተቆጣጠራት ሙዳጉ ግዛት ሀራርዳሬ በተባለ ስፍራ መሆኑ ታውቋል፡፡ ባለስልጣናቱ በተደረገው በዚህ የአየር ጥቃት ንጹሃን ሰዎች ያለመሞታቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

በፈረንጆቹ ህዳር 2017 ከተደረገው ተመሳሳይ እርምጃ የተሳካው መሆኑንም ወታደራዊ ባለስልጣናቱ አንስተዋል፡፡

አሜሪካ ከ24 ጊዜ በላይ የሰው አልባ የአውሮፕላን ጥቃት በአልሸባብ ላይ አድርሳለች፡፡ ሆኖም እርምጃው ቡድኑ አምና በተሸከርካሪ ባደረሰው ጥቃት የሞቱትን 500 ንፁሓን ከማሰብ ጋር ግንኙነት አንደሌለው  አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ዋሺንግተን ከዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በሶማሊያ ያላትን የጦር ኃይል ቁጥር 500 አድርሳለች፡፡ ሆኖም ፅንፈኛው ቡድን ከሞቃዲሾ ቢያፈገፍግም አሁንም ድረስ ደቡባዊና መካከለኛ ግዛቶች በብዛት ተቆጣጥሮ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ቡድኑ አስካሁንም በዋና ከተማዋና በተለያዩ ስፍራዎች ጥቃት ማደረሱን ቀጥሏል ሲል የዘገበው አልጀዚራ ነው፡፡