የሱዳን የሽግግር መንግስት በአደባባይ ከሚቃወሙ ዜጎች ጋር ተነጋገረ

የሱዳንን የሽግግር መንግስት ለማስተዳደር ቦታውን የተረከቡት ሌተናል ጄኔራል አብደልፈታህ አብዱልራህማን የሽግግር መንግስቱ ለሲቪል ባለስልጣን ይሰጥ በሚል ተቃውሞአቸውን ለማሰማት አደባባይ ከተሰለፉ ዜጎች ጋር ተናግረዋል፡፡

የሀገሬው አክቲቪስቶች እና ሌሎት ተቃዋሚዎች ግን የሲቪል የሽግግር መንግስት እስካልተቋቋመ ድረስ በአደባይ ተቃውሞአቸውን ማሰማት እንደሚቀጥሉ እየገለጹ ነው፡፡

ለአምስት ወራት የዘለቀው የሱዳን ህዝባዊ ተቃውሞ በስተመጨረሻ ለ30 አመታት ስልጣኑን ተቆናጠው የቆዩትን ኦማር አልበሽር ከስልጣን እንዲወርዱ አስችሏል፡፡

ተቃዋሚዎቹ ከአልበሽር መውረድ በኋላም መስመራቸውን ቀይረው በወታደራዊ መንግስት አንመራም በማለት አሁንም ድምጻቸውን እያሰሙ ነው፡፡

ከመፈንቅለ መንግስቱ በኋላ የሱዳን መከላከያ ሚኒስትርና የጦር ኃይል አዛዥ ጀነራል አዋድ ኢብን አዉፍ የሽግግር መንግስቱን ለሁለት አመታት በበላይነት እንደሚያስተዳድሩ ተገልጾ ቢቆይም በሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበዉ ከወታደራዊ ምክር ቤት ኃላፊነታቸዉ መነሳታቸዉን ይፋ አድርገዋል፡፡

የእርሳቸው መነሳት ተከትሎም ሌላኛዉ የመከላከያ አዛዥ ሌተናል ጀነራል አብደልፈታህ አብዱልራህማን በቦታው ተሰይመዋል፡፡

የሽግግር መንግስቱን በሀገሪቱ ተጥሎ የቆየው ሰአት እላፊ አንስቷል፡፡

ጄኔራል መኮንኑ የሽግግር መንግስቱ ለሲቪል ባለስልጣን ይሰጥ በሚል ተቃውሞአቸውን ለማሰማት አደባባይ ከተሰለፉ ዜጎች ጋር ተነጋግረዋል፡፡

የወታደራዊ ምክር ቤት ሀላፊነቱን የተረከቡት ጄኔራሉ የሀገሪቱን አስተዳደር ከሁለት አመታት በኋል ለሲቪል መንግስት እንደሚያስረክቡ ቃል ገብተዋል፡፡

ወታደራዊ ሀይሉ ከተቃዋሚዎች ጋር እንዲነጋገር ሲወተውቱ የነበሩትና የጦር ኃይሎች ድጋፍ ሰጪ ኃይል አዛዥ የሆኑት ሃማድ ዳጋሎ የአብድልፈታህ ምክትል ሆነው መሰየማቸው ተነግሯል፡፡

አብድልፈታህ ለሱዳን ህዝብ በመጀመሪያ የቴሌቪዥን ስርጭት ባስተላለፉት መልዕክታቸው መሰል ውይይቶች ሁሉንም የሱዳን ህዝብ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና ሲቪል ማህበረሰቦችን ባካተተ መልኩ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ ለመጪዎቹ ሁለት አመታት የወታደራዊ ምክር ቤቱ ሀገሪቱን እንደሚያስተዳድርም ተናግረዋል፡፡

አምስት ወራትን በዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ ዜጎች ላይ ጥቃት ሲያደርሱ የነበሩ አካላትን ለፍትህ ለማቅረብ እንደሚሰሩም ጄኔራል መኮንኑ ቃል ገብተዋል፡፡

የሀገሬው አክቲቪስቶች እና ሌሎች ተቃዋሚዎች ግን የሲቪል የሽግግር መንግስት እስካልተቋቋመ ድረስ በአደባይ ተቃውሞአቸውን ማሰማት እንደሚቀጥሉ እየገለጹ ነው፡፡

ወታደራዊ ሀይሉ ላይ እምነት ያላሳደሩት ዜጎቹ ለአልበሽር ታማኝ በነበሩ ሀይሎች የተሞላው ወታደራዊ ሀይሉ አሁንም ቢሆን በእጅ አዙር ስልጣኑን ሊቆናጠጥ እንደሚችል ያደረባቸውን ስጋት ገልጸዋል፡፡

ሁላችንም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሽግግር መንግስቱ በወታደራዊ ሀይሉ መያዙን እንቃወማለን፤ ሙሉ በሙሉ የሲቪል መንግስት እንዲያስተዳድረው ነው ፍላጎታችን ስትል የባታ ፓርቲ አባል የሆነቸው ሳላ ሳንሆሪ ተናግራለች፡፡

የሱዳን የሙያ ማህበር በበኩሉ ተቃዋሚዎች ለቀጣዮቹ ሰባት ቀናት ካርቱም በሚገኘው የወታደራዊ ሀይሉ ዋና መቀመጫ ፊት ለፊት ተቃውሞአቸው ማሰማት እንዲቀጥሉ አሳስቧል፡፡ /አልጀዚራ/