ኢትዮጵያና ጀርመን በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራረሙ

ኢትዮጵያና ጀርመን በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ አምስት የመግባቢያ ስምምነቶችን ተፈራረሙ፡፡

ከጀርመን ባቫሪያ ግዛት የተውጣጡ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብ ተወካዮችና ከስልሳ በላይ የንግድ ድርጅቶች የተሳተፉበት የኢትዮ-ጀርመን የንግድ ምክክር በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩም በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመነት አማራጭ አስመልክቶ ለተሳታፊዎች ገለጻ ተደርጓል፡፡

ትኩረታቸውን በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ያደረጉ አምስት የመግባቢያ ሰነዶች በኢትዮጵያና በባቫሪያ ግዛት መካከል መፈረማቸውን የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ደዋኖ ከድር የውጭ ኢንቨስትመንትን ከመሳብና ከማበረታታት አንጻር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ እየተመዘገበ የመጣው ለውጥ ተስፋ ሰጪ መሆኑን የገለጹት በጀርመን የባቫሪያ ግዛት አስተዳዳሪ ማርከስ ሶደር ለለውጡ ቀጣይነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉና በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሪት ሃና አርአያስላሴ በበኩላቸው ከውጭ ኢንቬስተሮች እንደተግዳሮት የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታትና የሀገሪቱን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሁኔታ አንዲሻሻል መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይነት የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብ በተለያዩ አማራጮች ላይ የማበረታቻ ስራዎች እንደሚከናወኑም ምክትል ኮሚሽነሯ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያና ጀርመን በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት እያጠናከሩ መምጣታቸው በመድረኩ ተገልጿል፡፡