በሱዳን የሟቾች ቁጥር 60 መድረሱ ተገለጸ

በሱዳን የሟቾች ቁጥር 60 መድረሱን ተቃዋሚዎች እያስታወቁ ነው፡፡

በሱዳን ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ህዝባዊ ተቃውሞ እንደ አዲስ መቀስቀሱን ተከትሎ ላለፉት ሁለት ቀናት ውጥረቱ አይሎ ነበር፡፡

ጊዜያዊው ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣን ለሲቪል ያስረክብ ያሉ ተቃዋሚዎች ጋር ግጭት ውስጥ የገባው  የፓርላማ ጥበቃ ቡድን የሰው ሕይወት አጥፍቷል ሲሉ ተቃዋሚዎች ይወነጅላሉ።

እንግሊዝ እና ጀርመን የተባበሩት መንግሥታት ወታደራዊው ጊዜያዊ መንግሥት መፍትሄ ያበጅ ዘንድ ተማፅነዋል፤ ቻይና እና ሩስያ በሱዳን ጉዳይ እያሤሩ ነው ሲሉም ወቅሰዋል።

የሱዳን መከላከያ ኃይል ዋና መሥሪያ ቤት ደጃፍ ሲደረግ የነበረው የመቀመጥ አድማ ለወራት የዘለቀ ቢሆንም ዕለተ ሰኞ የሆነው ግን ተቃዋሚዎች ያልጠበቁት ነበር። የሱዳን ልዩ ኃይል በአስለቃሽ ጋዝ በመታገዝ ሰልፈኞችን ይበታትን ያዘ።

ሰዳናውያን በአል-ባሽር ዘመን ጃንጃዊድ በሚል ስያሜ የሚታወቀው ልዩ ኃይሉ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተጠና እርምጃ ወስዷል ሲሉ ይከሳሉ።

ጊዜያዊው ወታደራዊ አገዛዝ በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ምርጫ ይካሄዳል የሚል መግለጫ ቢያወጣም ሱዳናውያን የአል-በሽር በሽታ ያልለቀቃቸውን ሰዎች ለማፅዳት ረዘም ያለ ጊዜ ያሻል ሲሉ ይሞግታሉ።

ወታደራዊው መንግሥት እና የነፃነትና የለውጥ ኃይል የተሰኘው ተቃዋሚ ቡድን ደርሰውት የነበረውን ስምምነት ጊዜያዊው አስተዳደር አፍርሶታል ይላል የቢቢሲ አፍሪቃው ተንታኝ ፈርጋል ኪን።

አክሎም ወታደራዊው መንግሥት ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ብርቱ ጫና እየደረሰበት አይደለም ባይ ነው ተንታኙ።

ወጣም ወረደ ሱዳናውያን የረመዳን ፆምን ከሚቃጠል ጎማ በሚወጣ ጭሥ ታጅበው፤ ሠላም እንደራቃቸው አሳልፈዋል፤ ፆሙንም የፈቱት አደባባይ ላይ ሆነው ነው።

ማሕበራዊ ድረ ገጾች ላይ የሚለቀቁ ምስሎች የሱዳን ወታደሮች መንገዶችን እንደተቆጣጠሩት የሚያሳዩ ናቸው።

የተመባበሩት መንግሥታት ወታደራዊው መንግሥት መፍትሄ እንዲያበጅ ከመማፀን ወደኋላ አላለም።/ቢቢሲ/