በአሜሪካ የመድኃኒት ዋጋ እየናረ ነው

የአሜሪካ መድኃኒት አምራቾችን ከመክሰስ ሰማይ ማረስ ይቀል ነበር። አሁን ግን ግዙፎቹ አምራቾች ይንገዳገዱ ይዘዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ከዚህ በኋላ መድኃኒት አምራቾች ምርታቸውን በቴሌቪዥን መስኮት ሲያስተዋውቁ ዋጋቸውን መጥቀስ የግድ ይላቸዋል ሲል አዟል።

ትራምፕ በምረጡኝ ቅስቀሳቸው ወቅት የመድኃኒት ዋጋን እቀንሳለሁ ሲሉ ቃል ገብተው ነበር፤ ለዚህ ሃሳባቸው ደግሞ ከሁለቱም አውራ ፓርቲዎች ድጋፍ አልተለያቸውም።

አንድ ጂሊያድ የሚባል ኩባንያ ባለቤት ለዚሁ ጉዳይ ይፈለጋሉ ተብለው ወደ ምክር ቤት ተጠሩ።

የዴሞክራቲክ ፓርቲ ተወካይ የነበሩት አሌክሳንድሪያ ኦካዚዮ – ኮርቴዝ አንድ ጥያቄ ሰነዘሩ። ለምን ይሆን ተመሳሳይ መድኃኒት አውስትራሊያ ውስጥ 8 ዶላር ሆኖ ሳለ አሜሪካውያን 2000 ዶላር (58 ሺህ ብር ገደማ) እንዲከፍሉ የሚጠየቁት? ሲሉ።

እርግጥ አጥጋቢ መልስ አላገኙም። «ሰዎች ያለምክንያት እየሞቱ ነው» ነበር የሴናተሯ መደምደሚያ።

ኮመንዌልዝ ፋውንዴሽን ያሠራው ጥናት እንደሚጠቁመው አሜሪካ መድኃኒትን በውድ ዋጋ በመሸጥ ከዓለም አንደኛ ናት።

በአማካይ አንድ አሜሪካዊ ለመድኃኒት ብቻ በዓመት 1200$ (34 ሺህ ብር ገደማ) ያወጣል። በሌላው ዓለም ግን ከ466 እስከ 939 ዶላር መሆኑን ጥናቱ ይጠቁማል።

ለምሳሌ አንድ የደም ካንሰር ያለበት አሜሪካዊ ለሕክምና 70 ሺህ ዶላር ሊያወጣ ይችላል። ወደ አሜሪካ ጎረቤት ሜክሲኮ ወረድ ሲባል ግን 2 ሺህ ዶላር ሆኖ ይገኛል።

ኢንሱሊን ካናዳ ውስጥ 38 ዶላር ይጠየቅበታል፤ በሌላ በኩል አንድ አሜሪካዊ 200 ዶላር ይከፍላል። ብዙ የማይገኙና ለየት ያሉ መድኃኒቶችማ ዋጋቸው የሚቀመስ አይደለም።

የአሜሪካ መድኃኒት አምራቾችን የሚወክል አንድ ተቋም የክንኒና ዋጋ እንዲህ ንሮ ይታይ እንጂ አሜሪካውያን ሙሉ ዋጋውን አይከፍሉም ሲል ይከራከራል።

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አብዛኛውን ወጪውን ስለሚሸፍኑ ግለሰቦች ላይ የሚደርሰው ጫና በአንፃሩ ቀለል ያለ ነው የሚል መከራከሪያ ያቀርባል።

ችግሩ ወዲህ ነው። 27 ሚሊዮን ገደማ አሜሪካውያን የኢንሹራንስ ባለቤት አይደሉም። ይህ ማለት ደግሞ ሙሉ ወጪውን መሸፈን የታካሚ ግዴታ ነው።

በብዙ የዓለም ሃገራት የሕብረተሰብ ጤና አገልግሎት ሰጪዎች አምራቾች ዋጋ እንዲቀንሱ አብዝተው ይሟገታሉ። አሜሪካ ውስጥ ይህ የሚታሰብ አይደለም።

የአሜሪካ የመድኃኒት ዋጋ ፍትሐዊ አይደለም ብለው የሚሞግቱ ሰዎች አንድ የሚያንገበግባቸው ጉዳይ አለ። ይህም ኩባንያዎቹ መድኃኒት የሚያመርቱት ከሕዝብ በተሰበሰበ ገንዘብ መሆኑ ነው።

ሴናተር ኦካዚዮ-ኮርቴዝ ያንገበገባቸው አንድም ይህ ነው። «እንዴት እኛው ለመድኃኒቱ መሥሪያ ከፍለን ይህን ያህል ገንዘብ እንጠየቃለን?» ሲሉ ነበር ጠጠር ያለች ጥያቄ የሠነዘሩት። (ምንጭ፡ ቢቢሲ)