የሶማሊያ መንግሥት የአገሪቱን ቱሪዝም ለማተኮር ማቀዱን  አስታወቀ 

ለረዥም ዓመታት በድርቅና በጦርነት ስትታመስ የኖረችው ሶማሊያ ፊቷን ወደ ቱሪዝም ለማዞር የሃገሪቱ መንግስት ሃገሪቱን ቱሪዝም እንዱስትሪ የማደስ አላማ እንዳለው አስታወቀ፡፡

ከአፍሪካ ቀንድ ብሎም በአለም በድርቅና በጦርነት ስሟ የሚነሳው ሶማሊያ ከዚህ አዘቅት እንድትላቀቅ የአለም ሃገራት የተለያየ አይነት እርዳታ ሲያደርጉላይ እንደነበረ የሚታወስ ነው፡፡

የሶማሊያ የመረጃ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ አብዱራህማን ኡመር ኦስማን ያሪሶ በሃገረ ስፔን ባደረጉት ንግግር ላይ ነው በውድቀት ላይ የሚገኘው የሃገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥተው ለመስራት እየጣሩ እንደሆነ የተናገሩት፡፡

እስከ እኤአ 1990ዎቹ ድረስ የሃገሪቱ የቱሪዝም ሴክተር  ከፍተኛ የገቢ ምንጮች ከሚባሉ መካከል አንዱ የነበረ ሲሆን የሃገሪቱ የቀድሞ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዚያድ ባሬ የሥልጣን ዘመን ብኋላ  የአፍሪካ ቀንድ ላይ የምትገኘው ሶማሊያ በዓለም ላይ ከሚገኙ ሃገራት መካከል ለረዥም ዓመታት በግጭትና በድህነት የምትታወቅ ሃገር ሆናለች፡፡

የሶማሊያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሩ በዱራህማን ኦማር ኡስማን ስፕን ለጉብኝት በሄዱበት ወቅት የአለም የቱሪዝም ኦርጋናይዜሽን  ዋና ፀሃፊ ሚስተር ታሊብ ዲ ራፋይና ከሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው የሶማሊያ የቱሪዝም ሴክተሩን ለማነቃቃት ተባብረው መስራት እንዳለባቸው ተወያይተዋል፡፡

ከስፔን መንግስት ጋር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር የሚቻልባቸውን መንገዶች ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይም ተወያይተዋል፡፡

አልሸባብ ከሶማሊያ ዋና ከተማዋና በዙሪያዋ ካሉ ቦታዎች መልቀቁ የሃገሪቷ መንግስት የቱሪዝም ሴክተሩን ለማደስ የሚያደርገው እንቅስቃሴ  ላይ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

 በዚህም በታቀደው መሰረት በዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ የሚገኘው የባህር ዳርቻ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግም የሃገሪቱ መንግስት በጥረት ላይ እንደሆነ ገልጿል ፡፡

በአካባቢው የሚኖሩ ነጋዴዎች ወደ ስራቸው በማተኮር አዳዲስ ሆቴሎችንና የእንግዳ ማረፊያዎችን በመክፈት እና ከውጭ ለሚመጡ እንግዶች የምዕራባውያን ምግብ በማዘጋጀት የቀድሞዋን ሶማሊያ ለመመለስ በጥረት ላይ ናቸው ተብሏል፡፡