ኢራን በሶርያ በሚንቀሳቀሰው አይ ኤስ ላይ የሚሳኤል ጥቃት ሰነዘረች

ኢራን በሶርያ በሚንቀሳቀሰው አይ ኤስ ላይ የሚሳኤል ጥቃት ሰነዘረች፡፡

ጥቃቱ በቴህራን ለተፈፀመው የሽብር ጥቃት የአፀፋ በቀል ነው ተብሏል፡፡ ኢራን ወደ ሌላ አገር ሚሳኤል ስታወናጭፍ በ30 ዓመት የመጀመሪያው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የበሽር አላሳድን መንግስት ትደግፋለች በሚል በተደጋጋሚ የምትወቀሰው ኢራን በሶርያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን አሸባሪ ቡድን አይ ኤስን ኢላማው ያደረገ የሚሳኤል ጥቃት መሰንዘሯ ተጠቁሟል፡፡

ጥቃቱ በፈረንጆቹ ሰኔ ሰባት ቀን 2017 ስድስት ዜጎቿን ለሞትና 16ቱን ለአካል ጉዳት ለዳረገው በአሸባሪ ቡድኑ ለተሰነዘሩባት ሁለት ጥቃቶች የአፀፋ ምላሽ ነው ተብሏል፡፡

በኢራን ፓርላማ ህንፃና በኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላህ ሆሜኒ ስም በተሰየመው ቅዱስ ስፍራ ለተፈፀመው የሽብር ጥቃት አይ ኤስ ኃላፊነት መውሰዱ ይታወቃል፡፡

ይህን ተከትሎም  ቴህራን ከአይ ኤስ ጀርባ የሳዑዲ አረቢያ እጅ ሳይኖርበት አይቀርም በሚል ወቀሳ አቅርባለች፡፡

ኢራን በሌላ አገር ላይ ሚሳኤል ስታወናጭፍ ከሶስት አሰርት ዓመታት በኋላ የመጀመሪያው መሆኑም ነው የተገለፀው፡፡ ቴህራን  ዞልፋካር ኤም አር ቪ የተሰኙ ስድስት ዘመናዊ ሚሳኤሎችን ለጥቃት ሰንዝራለች፡፡

መካከለኛ ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤሎቹ ከምዕራብ ኢራን ከርማንሻህ ግዛት ነው የተወናጨፉት፡፡ ዋና ዓላማቸውም በምስራቅ ሶርያ ዴር ኢዞር በሚባለው አካባቢ የሚንቀሳቀሰውን ታክፊር የተሰኘውን አሸባሪ ቡድን እንደሆነ ተመለክቷል፡፡

ፅንፈኛው አሸባሪ ቡድን አይ ኤስ በኢራን ታክፊር የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ዘገባው አስታውቋል፡፡

የሲ ኤን ኤን የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኝ ሌቴናል ኮሎኔል ሪክ ፍራንኮና በቴህራን ላይ የሽብር ጥቃት የሰነዘሩ ፅንፈኞችን ዒላማው ያደረገው የኢራን የሚሳኤል ጥቃት ግቡን መምታቱን ተናግረዋል፡፡ ለሶርያ ወታደሮችም ትልቅ መነቃቃትን መፍጠሩን ነው ጨምረው የገለፁት፡፡

ኢራን በአይ ኤስ ላይ የወሰደችው የአፀፋ ጥቃት በቴህራን ለደረሰው የሽብር ጥቃት በቀል መሆኑን ጠቁማ ከቴህራን የሽብር ጥቃት በስተጀርባ የሳዑዲ አረቢያ እጅ አለበት የሚለውን ክስ አሁንም አጠናክራ ቀጥላለች፡፡ ሳዑዲ ከዚህ ድርጊቷ እንድትታቀብ በማሳሰብ፡፡

ሳዑዲ አረቢያና አጋሮቿ ኳታር አክራሪዎችን ትደግፋለች በሚል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማቋረጣቸው ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎም ኢራን ከኳታር ጎን በመሰለፍ የአየር  ክልሏን በመፍቀድ አጋርነቷን አሳይታለች፡፡ ታክፊርን ከሶርያ ለማውጣት የምታደርገው ጥረት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቃለች፡፡