ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ የምስራቅ አፍሪካ ጉብኝታቸውን ጀመሩ

የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲስ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት በታንዛኒያ ጀመሩ፡፡

አል ሲስ በኬንያ፣ ኡጋንዳና ታንዛኒያ በሚኖራቸው ቆይታ በንግድና ምጣኔ ሃብት ላይ ትኩረት አድርገው ይወያያሉ፡፡

በግብጹ ፕሬዝዳንት በአፍሪካ ሀገራት  ጉብኝት ሲያደርጉ የአሁኑን ጨምሮ ለአስራ አንደኛ ጊዜያቸው ነው፡፡

ይህ ደግሞ ፕሬዝዳንቱ ቀደምት በስልጣን ላይ የነበሩ የግብጽ መሪዎች ከአፍሪካዊያን ሀገራት ጋር ተራርቀው የቆዩበትን የግንኙነት መንፈስ ለመቀየር ያለመ እንደሆነ ነው የሚነገረው፡፡

የአሁኑ የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ትኩረት አድርጓል፡፡

አልሲስ በቅድሚያ ታንዛኒያን እየጎበኙ ሲሆን በዳሬሰላም የሁለት ቀን ቆይታ ይኖራቸዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በታንዛኒያ ቆይታቸው ግብጽ በተለይ ከታንዛኒያ ጋር ስለሚኖራት የንግድና የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ የመጀመሪያ አጀንዳ አድርገው ይመክራሉ ተብሏል፡፡

ግብጽ መላ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን እያሳዩበት ያለውና በመተባበር የሚገነቡትን ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታን በዚህ ጉብኝት ላይ ከየሀገራቱ ጋር  ሃገሪቷ ያላትን አቋም ለማሳወቅ እንዲሁም ሀገራቱ ድጋፍ እንዲሰጧት ለማድረግ እንደምትጠቀምበትም ተነግሯል፡፡

ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የዚህ ግድብ ግንባታ ሲከናወን የተፋሰሱን ሀገራት በማይጎዳና የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጥ መልክ መሆኑን በተደጋጋሚ ለማስረዳት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እያደረገች ነው፡፡

ይሁን እንጅ ግብጽ አሁንም ድረስ ኢትዮጵያ ግድቡን በአባይ ወንዝ ላይ መገንባቷ ወደ ሀገሪቱ የሚፈሰው የውሃ መጠን ይቀንሳል የሚል አቋም እስካሁን ይዛለች፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አል ሲሲ በቆይታቸውም ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ስጋት የሆነውን የሽብር ድርጊትን በተመለከተ እንዲሁም የደህንነት ጉዳዮች ላይም ከሀገራቱ መሪዎች ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡