ኬንያ ጂጂታል የሆነ የአሽከርካሪዎች መንጃ ፈቃድን በተግባር ልታውል ነው

ኬንያ በተያዘው የፈረንጆች ጥቅምት ወር ላይ ድጂታል የሆነ የአሽከርካሪዎች መንጃ ፈቃድ  በተግባር ላይ ልታውል መሆኑ ተነገረ፡፡

የኬንያዊያን አሽከርካሪዎች ከዚህ ወር አንስቶ የመንጃ ፈቃዳቸው ዲጂታል እንደሚሆን ነው የዴይሊ ኔሽን ዘገባ ያመለከተው፡፡

በዚህም መሠረት በወረቀት ደብተር ላይ የነበረው የመንጃ ፈቃድ ወደ ስማርት ካርድነት ይለወጣልም ነው ያለው ዘገባው፡፡

የኬንያ ብሔራዊ የትራንስፖርትና ደህንነት ባለስልጣን እንዳስታወቀው በመጀመሪያው ዙር ለአሽከርካሪዎች የሚሠራጭና ለዚሁ አገልግሎት የሚውል አስር ሺህ ስማርት ካርዶች ተዘጋጅተዋል፡፡

እነዚህ ስማርት ካርዶች የፍጥነት ወሰንን የሚጥሱና ሌሎች ህጎችን የሚተላለፉ አሽከርካሪዎችን ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያስችል ሶፍትዌር የተጫነለት ነውም ተብሏል፡፡

የኬንያ ብሄራዊ የትራንስፖርትና ደህንነት ባለሥልጣን ዳይሬክተር ፍራንሲስ ማጃ እንደገለጹት ዲጂታል የመንጃ ፈቃዱ በዚህ ተግባር ላይ እንዲውል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡

ከዚህ ቀደም የነበረው አሠራር የትራንስፖርት ህጉን የሚጥሱ አሽከርካሪዎችን ማንነት ለመለየት አዳጋች ስለነበር በሰዎች ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ አሽከርካሪዎች የሚሠወሩበት ሁኔታዎች ያጋጥሙ እንደነበር ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡

አዲሱ አሠራር ተግባራዊ ሲሆን ግን ህግ የተላለፈውን አሽከርካሪ ለመለየት ቀላል ከመሆኑም በላይ ህግን በመጣስ የሚከሰቱ አደጋዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል ነው የተባለው፡፡

የዲጂታል የመንጃ ፈቃዱ ተግባራዊ ሲሆን የፍጥነት ወሰንን ተላልፎ ሲያሽከረክር ሆነ ሌሎች ህጎችን  ሲጥስ የተገኘ አሽከርካሪ ከ500 እስከ 10 ሺህ የኬንያ ሺልንግ ቅጣት ይጠብቀዋል ሲል የዘገበው ዴይሊ ኔሺን ነው፡፡