ሱዳን ህገወጥ የጦር መሣሪያ የማስፈታት ዘመቻን የሚያደናቅፉት ላይ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠነቀቀች

ሱዳን የጀመረችውን ህገወጥ የጦር መሣሪያ የማስፈታት ዘመቻ ለማደናቀፍ በሚንቀሳቀስ ማንኛውም አካል ላይ የሞት እርምጃ እንደምትወስድ የሃገሪቱ ምክትል ፕሬዚደንት አስጠነቀቁ፡፡

ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር ሱዳን ዳርፉርና ኮርዶፋን በሚባሉ ሁለት የሀገሪቷ ግዛቶች የሚከሰቱ የእርስ በርስ ግጭቶች በርካታ ዜጎቿን ለሞት ከመዳረጋቸውም በተጨማሪ አካባቢዎቹ ሰላም የራቃቸው እንዲሆኑ አድርጎቸዋል፡፡

በሁለቱ አካባቢዎች ከሚገኙ ሱዳናዊያን መሃል ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉት ደግሞ በህገወጥ መንገድ የጦር መሣሪያ የታጠቁ በመሆናቸው ችግሩን የከፋ አድርጎት ቆይቷል፡፡

አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ በዳርፉር አንድ መቶ ሰላሳ አምስት ሰዎች ሲገደሉ በኮርዶፋን ደግሞ ሰማንያ ዘጠኝ ዜጎች በህገወጥ ታጣቂዎች ተገድለዋል፡፡

ታዲያ ይህ የርስ በእርስ ግጭትና የህገወጥ ታጣቂዎች ቁጥር መበራከት ከፍተኛ የራስ ምታት ሆኖበት የቆየችው ሱዳን በመጨረሻ በተደራጀ ዘመቻ ህገወጥ ትጥቅን ማስፈታት አማራጭ የለሌለው መፍትሄ መሆኑን በማመን ወደ ተግባር ተሸጋግራለች፡፡ 

እስካሁን በተደረገው ህገወጥ መሳሪያ የማሰባሰብ ሂደት ዉጤቶች ማስመዝገብ ቢቻልም ሂደቱን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ክስተቶች ግን ዘመቻው በተሳካ ሁኔታ እንዳይጠናቀቅ እንቅፋት መሆናቸው አልቀረም፡፡

ከእነዚህ እንቅፋቶች መካከል ጥቂት የማይባሉ አካላት ህገወጥ የጦር መሣሪያ ትጥቅን የሚያበረታቱና ታጣቂዎቹ የጦር መሣሪያቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዳያስረክቡ የሚያነሳሱ ቅስቀሳዎችን በህቡዕ እና በግልጽ ማድረጋቸው ይጠቀሳል፡፡

በዚህ አሉታዊ ቅስቀሳ የተቆጣው የሱዳን መንግስት በዳርፉርና ኮርዶፋን የተቋቋመው ትጥቅ አስፈቺ ግብረ ኃይል በእነዚህ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ሙሉ ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡

ከሱዳን ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክተው ሃገሪቱ የጀመረችውን  ህገወጥ የጦር መሳሪያ የማሰባሰብና ትጥቅ የማስፈታት ስራ ለሚቃወም አካል ምንም አይነት ምህረት የላትም፡፡

የሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንትና የህገወጥ መሳሪያው አስመላሽ ግብረ ሃይል አለቃ ሀሻቦ ሞሃመድ አብደል ራህማን እንደገለጹት ግብረ ኃይሉ በነዚህ አካላት ላይ እስከመግደል የሚደርስ እርምጃ እንዲወስድ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

አብደል ራህማን በመግለጫቸው እነዚህ አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል ብለዋል፡፡

እነዚህ አካላትን በቁጥጥር ስር ከማዋል አንስቶ የሃገሪቱ ህገ መንግስት ያጎናጸፋቸውን መብት እስከመግፈፍ የሚያደርስ እርምጃ ይወሰድባቸዋል ብለዋል ምክትል ፕሬዝዳንቱ፡፡ 

ከላይ እየተወሰደ ካለው እርምጃ በተጨማሪ ህገወጥ የጦር መሳሪያዎች ወደ ሱዳን ይገቡባቸዋል የተባሉ ስልሳ ሶስት መንገዶች ሙሉ በሙሉ መዘጋታቸወም ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል፡፡