ደቡብ ሱዳን በነዳጅ ምክንያት የሚደርስባት ብክለት እንዳሳሰባት ለመንግሥታቱ ድርጅት አስታወቀ

ደቡብ ሱዳን በነዳጅ ምክንያት እየተበከለባት ያለውን የውሃ ክፍል አስመልክቶ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተማጽኖ ደብዳቤ ማስገባቷ ታውቋል፡፡

አገሪቱ ማመልከቻውን ያስገባችው ሁሉም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል አገራት ተወካዮች በተገኙበትና  በኬንያ ናይሮቢ የአካባቢ ጥበቃን አስመልክቶ እየተደረገ ባለው ስብሰባ ላይ ነው፡፡

በአገሪቱ በሚገኙና በተመረጡ የነዳጅ ማምረቻዎች ላይ በተደረገ ጥናት አከባቢዎቹ መርዛማ በሆኑት ሊድ እና ባሪየም ንጥረ ነገሮች እየተበከሉ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡በጣም አደገኛ የሆነው ብክለት ደግሞ በአገሪቱ ኮች የተባለው ስፍራ ላይ ተስተውሏል፡፡

አካባቢው ከነዳጅ ማምረቻው በ22 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቢገኝም ችግሩ በጎላ መስተዋሉ ነው የተነገረው፡፡አካባቢው በመርዛማ ንጥረ ነገሮቹ ይበከላል ተብሎ ከተጠበቀው 4 እጥፍ በላይ መሆኑም እያነጋገረ ይገኛል፡፡

ታዲያ በመርዛማ ንጥረ ነገሮቹ የተስተዋለው የውሃ ብክለት ደቡብ ሱዳናዊያን ለከፋ የጤና ችግር እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል ተብሏል፡፡ለደም ማነስ ፣ኩላሊት እና ለነርቭ በሽታ እየተጋለጡ መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎችም ከዚህ ላለፈ የአካል እና የስነ ልቦና በሽታ አጋላጭ በመሆኑ ትኩረት እንደሚያሻው ገልጸዋል፡፡

ለችግሩ ተጠያቂ መሆን የነበረባቸው አለም አቀፍ ነዳጅ አምራቾች በቸልታ እየታለፉ መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል፤የደቡብ ሱዳን መንግስት ከእነዚህ አለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር ከባለፈው አመት ጀምሮ ውይይት እያደረገ ቢሆንም ችግሩ ቀጥሎ በብክለቱ የሚጎዱ ዜጎችም መፍትሄ አጥተዋል፡፡.

አሁን ደግሞ አገሪቱ አለም በነዳጅ ምርት ሂደት ምክንያት እየተበከለባት የሚገኘውን የውሃ ክፍሏን መታደግ እንዲችል በማመልከቻ ጠይቃለች፡፡ጆሴፍ ባርቴል የተባሉ  የደቡብ ሱዳን መንግስት መልክተኛ ማመልከቻውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስለ አከባቢ ጥበቃ ሁሉም አባል አገራት ተሳታፊ በሆኑበት ስብሰባ ላይ አቅርበዋል፡፡

ማመልከቻው ደቡብ ሱዳን ነዳጅ ባስከተለባት የአከባቢ ብክለት ሙከራ ውስጥ ናት ብሏል፡፡እርዱን አጽዱልን የሚል ጠንካራ መልዕክት የተነበበት ደብባቤ የተመድ አከባቢ ጥበቃ ሰዎች እጅ  ደርሷል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ አመታት ይህ  በሰብአዊ መብት እና አከባቢ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ወጀል ሳይንቲስቶች ለማስረዳት የለፉበት ጥረታቸው በአለም ማህበረስብ ዘንድ ግንዛቤ እየፈጠረ ነው ተብሏል፡፡

ክላዉስ ስትግሊዝ የደቡብ ሱዳን የነዳጅ አከባቢ ብክለት ደረጃን ለአለም እያስዋቁ ካሉ መንግስታዊ ድርጅቶች ያንዱ ሀላፊ ሲሆኑ የደቡብ ሱዳን መንግስትም ሆነ ሌሎች አገራት ችግሩ በሰዎች ጤና እና በውሃ አካል ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በውል የተረዱት አይመስሉም ወይም እንዳላየ ማለፍን ምርጫቸው ሳያደርጉ አልቀሩም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡

አሁን ግን ማመልከቻውን ተከትሎ የነዳጅ ምርትን በማምረት ሂደት  የተበከችው ደቡብ ሱዳን በሰፊው ትጸዳለች ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡

መርዛማ ንጥረ ነገሩ በምን ያህል ደረጃ  በሰዎች ላይ እየተገኘ ነው በሚል ታር ጃዝ የተባለ ነዳጅ አምራች ኩባንያ አቅራቢያ 96 ፈቃደኛ ሰዎች ጸጉራቸው ተወስዶ በተደረገ የናሙና ጥናት ሁሉም ከፍተኛ ነው በተባለ ደረጃ የነዳጅ ምርት ሂደት የተከሰቱት ሊድ እና ባርየም የተባሉት መርዛማ ንጥረ ነገሮች ተገኝተውባቸዋል፡፡

ደቡብ ሱዳን 2011 እንደ አገር ስትቋቋም አብዛኛውን የነዳጅ ሀብት ባለቤትነት ድርሻ ወስዳለች፡፡የነዳጅ ምርቷን በሱዳን በኩል ብቻ ነው የምትሸጠው፡፡በነዳጅ ሽያጭ ብቻ ለምትተዳደረው ደቡብ ሱዳን የተከሰተው የነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆል አገሪቱ ላለችበት ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀወስ አንደ አቀጣጣይ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

እንደ ደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ገለጻ በሱዳን በኩል በተዘረጋው የነደጅ መስመር ለአለም በቀን የሚያቀርቡት 350 ሺህ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ

ከአውሮፓውያኑ 2012 ወዲህ ለመስመሩ ከሚከፈለው ክፍያ ጋር ተያይዞ መግባባት ላይ ባለመደረሱ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡ ( ምንጭ:  የሱዳን ትሪቡን )፡፡