ቻይና በድጋሜ የዓለማችንን ፈጣን ባቡር በመስራት ወደ ስራ ሊገባ ነው

በቻይና ከቤጂንግ እስከ ሻንጋይ ከተሞች ተዘርግቶ የነበረው ፈጣን የባቡር መስመር ላይ አደጋ ከደረሰ በኋላ ፍጥነቱን የቀነሰበት ሁኔታ ነበር፡፡

አሁን ግን ችግሮቹን በመቅረፍም የአለማችንን ፈጣን ባቡር በዚው መስመር ላይ ስራውን ሊጀምር ነው፡፡

የዚህ የአዲሱ ትውልድ ፈጠራ አካል የሆነው ባቡር በቀጣይ የፈረንጆች ወር ከቻይና ዋና ከተማ ወደ ሻንጋይ በሚያደርገው የ1 ሺ 250 ኪሎሜትር መስመር ሲሆን የባቡሩ ፍጥነትም 350 ኪሎሜትር በሰአት በመሆኑ ከቤጂንግ ወደ ሻንጋይ የሚደረገው ጉዞ 4 ሰአት ከ30 ደቂቃ የሚፈጅ ይሆናል ሲል የዢንዋ መረጃ ያመለክታል፡፡ ይሄ ባቡር ስራውን እስኪጀምርም ጉዞው 6 ሰአታትን ይወስዳል፡፡

ቻይና በዚህ ፍጥነት የሚጓዝ ባቡር ስትሰራ የመጀመሪያዋ አይደለም፡፡ እ.ኤ.አ በ2008 በተመሳሳይ ፍጥነት የሚሄድ ባቡር ብትሰራም በ2011 በዌንዦ ከተማ አካባቢ ለ40 ሰዎች ሞት እና 191 ሰዎች ጉዳት ምክንያት ከሆነው የሁለት ባቡሮች ግጭት በኋላ ፍጥነቱን ከ250 አስከ 300 ኪሎ ሜትር በሰአት እንዲሄድ ተደርጎ ነበር፡፡

ቻይና በአሁኑ ሰአት 20 ሺ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የፈጣን ባቡር መስመር ያላት ሲሆን ይህም የዓለማችን 60 በመቶ የሚሆነው የፈጣን ባቡር መስመር ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2020 ተጨማሪ 10 ሺ ኪሎ ሜትር ለመዘርጋት ሀገሪቱ አቅዳ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡

አሁን ባለው ሁኔታም ለፈጣን የባቡር ሥራዎች 360 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ማድረጓን ተከትሎ ቻይና በዘርፉ የዓለማችንን ከፍተኛ በጀት የመደበች ሀገር ሆናለች፡፡ ሻንጋይ የንግድ ከተማ በመሆኗም የዚህ ባቡር ስራ መጀመር ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይገመታል፡፡     

የባቡሩ አጠቃላይ ስራም የሚካሄደው በቻይና ሲሆን የቻይና የባቡር ኮርፖሬሽን ስራውን የሚመራ ይሆናል፡፡ ( ምንጭ:  ሲሲቲቪ )