ኡጋንዳ በቻይና የገንዘብ ብድርና ድጋፍ የነዳጅ ምርቷን ለዓለም ገበያ ልታቀርብ ነው

ኡጋንዳ ከቻይና የገንዘብ ብድር እና ድጋፍ በመውሰድ ያላትን የተፈጥሮ ነዳጅ  እና ጋዝ ሀብት ለማልማት ከስምምነት ላይ የደረሰች ሲሆን  እ.ኤ.አ አቆጣጠር በ 2020 የነዳጅ ምርቷን ለአለም ገበያ እንደምታቀርብ ይፋ አድርጋለች፡፡

የምስራቅ አፍሪካዋ ኡጋንዳ  ቻይና  በሀገረ ምድሯ ላይ በነዳጅ እና በጋዝ ማውጣት ኢንደስትሪው ዘርፍ ላይ ይበልጡን ኢንቨስት እንድታደርግ ትፈልጋለች፡፡

ኡጋንዳ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በተሻለ በ 2020 የኢነርጂ ኃይል ምርት ያላት ሀገር ለመሆን የያዘችዉ ግብ  ለማሳካት እና  አቅም ለመገንባት ተጨማሪ ካፒታል ትፈልጋለች፡፡

ታዲያ ለዚህ ግብ መሳካት ቻይና የኡጋንዳን የገንዘብ ችግር በመቅረፍ ትልቁን ሚና ትጫወታለች፡፡

እ.ኤ.አ. በ 2018  ኡጋንዳ  የነዳጅ  ዘይት ማስተላለፊያ ቱቦዎችን ፣ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካዎችን ፣ የማዕከላዊ  ማምረቻ መሳሪያዎችን  እንዲሁም የነዳጅ የማጠራቀሚያ ገንዳዎችን  ለመገንባት በዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡

ኡጋንዳ እነዚህን እቅዶቿን እና እንቅስቃሴዎች በቀጣዮቹ ሶስት እና አምስት አመታት ውስጥ ለማሳካት 15 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋታል፡፡

እናም ኡጋንዳ ይህን የገንዘብ አቅም ለማግኘት በፕሮጀክቱ ላይ ቻይና ተሳታፊ እንድትሆን እና በተፈጥሮ ነዳጅና ጋዝ ዘርፉ  ውስጥ ያላትን ልምድ ተጠቅማ የአገሪቱን እቅድ እንድታሳካ ጋብዛታለች፡፡

ቻይና  በአሁኑ  ሰአት በኡጋንዳ ዋና  ዋና  መሠረተ  ልማት ፕሮጀክቶች ላይ መዋለ ንዋይዋን እያፈሰሰች ሲሆን ከእነዚህም  መሰረተ ልማቶች መካከል  በሃይድሮሊክ ኤሌክትሪክ ግድቦች ፣ በዋና  ዋና  የጎዳና መንገዶች  ግንባታ እንዲሁም በኡጋንዳ መደበኛ ደረጃ   የባቡር መንገድ ግንባታ ላይ ቻይና ትልቅ አስተዋፅኦ  እያደረገች ነው፡፡

የኡጋንዳ መንግስት እንዳረጋገጠዉ ሀገሪቱ 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ድፍድፍ የበርሜል ነዳጅ እና 5 መቶ ኪዩቢክ የተፈጥሮ ጋዝ ወይም ከ 5 ሚሊየን 2 መቶ ሺ ሊትር በላይ የቤንዚን ሀብት እንዳላት ይፋ አድረጓል፡፡

ይሁን እንጂ በአለም አቀፉ ደረጃ በየጊዜው የሚለዋወጠዉ  የነዳጅ ዋጋ  በዩጋንዳ ተወዳዳሪነት ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል  የገበያ  ተንታኞች እና አጥኚዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ያለው የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ 54 ዶላር ነው፣ ይህም ዋጋ ደህና እንደሆነ የሀገሪቱ የባንክ ባለሙያዎች የተናገሩ ሲሆን  በምዕራባዊ  ኡጋንዳ ውስጥ ካለው የተፈጥሮ ነዳጅ ሀብት ውስጥ 8 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው በአሁኑ ሰአት የተገኘዉ፡፡

ይህ ማለት እ.ኤ.አ. በ 2020 ኡጋንዳ ነዳጁን ወደ ማምረቱ ስትሸጋገር ተጨማሪ  ነዳጅ ያለባቸዉ ቦታዎች በአሰሳ ሥራዎች ሊገኙ እንደሚችሉ  የሀገሪቱ መንግስት ጠቁሟል፣ ስለዚህ ኡጋንዳ በአለም ገበያ ተፎካካሪነቷ አይቀንስም ፡፡( ምንጭ:  ሲ ጂ ቲ ኤን)