ህብረቱ 50 ሺህ የአፍሪካ ስደተኞችን ወደ አውሮፓ ለማስገባት የሚያስችል ዕቅድ ይፋ አደረገ

የአውሮፓ ህብረት 50ሺ የአፍሪካ ስደተኞችን ወደ አህጉሪቱ ለማስገባት የሚያስችለውን አቅድ ይፋ አድርጓል፡፡

ህብረቱ ባወጣው የሁለት አመት እቅድ ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡

ይህ በሊቢያ የባህር ጠረፍ አካባቢ ያለ ስደተኛ የተናገረው ነው፡፡ የሊቢያ በረሃን ለማቋረጥ የሚሞክሩ ስደተኞች በሽብር ቡድኑ አይ ኤስ ከመገደል ጀምሮ ገሚሶቹ በጀልባ መሥጠም ባህር ላይ ሲቀሩ አንዳንዶች ደግሞ በድካምና ረሃብ መንገድ ላይ ህይወታቸው ያልፋል፡፡ ይህ የህገወጥ ስደት አስከፊው ገጽታ ነው፡፡

ይህን አሳሳቢ ጉዳይ ለመግታትም የአፍሪካ ሃገራት ከአውሮፓ ህብረት ጋር በመተባበር ስራዎችን እየሰሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ 

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ሰሞኑን እንዳስታወቀው 50ሺ የአፍሪካ ስደተኞችን ወደ አውሮፓ ሃገራት ለማስገባት የሚያስችለውን አቅድ ይፋ አድርጓል፡፡

የህብረቱ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነር ዲሚትሪስ አቭራሞፖውሎስ የተዘጋጀው ዕቅድ እጅግ ውስብስብ እየሆነ ለመጣው የህገወጥ ስደት ችግር እልባት ለመስጠት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።  በአፍሪካ ያለውን ስር የሰደደ ህገወጥ ስደት እቅዱ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ይሆናል ብለዋል፡፡

ህብረቱ ባወጣው የሁለት አመት እቅድ ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ከአፍሪካ 50ሺ ስደተኞችን ተቀብሎ ለማስተናገድ በወጣው የህብረቱ እቅድ ሊቢያ፣ግብጽ፣ ኒጀር ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ቻድ ተካተዋል፡፡

የአውሮፓ ህብረት በእነዚህ ሃገራት የሚሰደዱ ዜጎችን ለማቋቋም የሚያስችል 587 ሚሊዮን ዶላር መድቧል፡፡ 

ዕቅዱ በህገ-ወጥ ደላለሎች ህይወታቸው አደጋ ላይ ለወደቁ ስደተኞች ደህንነታቸው ለማስጠበቅ ህብረቱ ከጀመራቸው ሥራዎች አንዱ ነው ተብሏል።

ዕቅዱ ስደተኞች በደረሱበት ሃገር ጥገኝነት መጠየቅ አለባቸው የሚለውን የአውሮፓ ሃገራት ህግ ያስቀረ ነው። ይህም ወደ አውሮፓ ለሚገቡ ስደተኞች እንደ መግቢያ የሚጠቀሙባቸውን የጣሊያንና የግሪክን ጫና እንደሚቀንሰው ታምኖበታል፡፡

የአውሮፓ ህብረት እስካሁን 23ሺ ስደተኞችን ከተለያዩ የስደተኞች መጠለያ አውጥቶ እንዲቋቋሙ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም አውሮፓ ህብረት ስደተኞች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ የሚያደረገውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት፡፡

የህብረቱ አባል ሃገራት ተወካዮች በተገኙበት በተደረገው ምክክር ሃገራት ስደተኞችን እንዲቀበሉ የተያዘውን እቅድ ሁሉም ሃገራት ሲቀበሉት ፖላንድና ሃንጋሪ ብቻ መቃወማቸው ተነግሯል፡፡

አዲሱ የሁለት ዓመት ዕቅድ የመካከለኛው ምሥራቅና ቱርክን ከማካተቱም በተጨማሪ ለሰሜንና የምሥራቅ አፍሪካ ሃገራት ዜጎች ትኩረት መስጠቱ የተለየ ያደርገዋል ተብሏል፡፡ ዘገባው የአልጀዚራ ነው፡፡