ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞ የአገሪቱ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ የነደፉት የጤና መድህን ፖሊሲ ማክተሙን ተናገሩ

የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው የድምፅ  አሠጣጥ ሂደት የቀድሞ የጤና ፖሊሲ 217 ለ 213 በሆነ ጠባብ የድምፅ ልዩነት ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ ኮንግሬስ ያሉ ዲሞክራቶች ባለፉት ሰባት ዓመታት ቃል በገቡት መሠረት ኦባማ ኬር እየተባለ የሚጠራው የጤና መድህን ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን ብዙ ደክመዋል፤ ብዙ ርቀትም ተጉዘዋል፡፡

በቀድሞው የሃገሪቱ ፕሬዚዳንት ጠንሳሽነት የተዘጋጀው ይህ የጤና  ፖሊሲ  የጤና መድህን ያልነበራቸው ብዙ አሜሪካውያን በተመጣጣኝ ዋጋ የጤና ጥበቃ አገልግሎት ማግኘት እንደሚያስችላቸው ሲነገር ቆይቷል።

እኤአ ከ2010 ጀምሮ 20 ሚሊየን የሚሆኑ አሜሪካውያን የጤና መድህን ዋስትናን ለማረጋገጥ አሜሪካ ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ8 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጓል፤ ይህ አሃዝ ታዲያ ብክነት የተንፀባረቀበት በሚል በአዲሱ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አልተወደደም፡፡

 

አዲሱ እቅድ የጤና ጥበቃ ወጪዎችን ይጨምራል በሚል ዴሞክራቶች ሲቃወሙት ቢከርሙም ትናንት በተሠጠ ድምፅ ዲሞክራቶች ብዙ ሲሰብኩለት የነበረው “ኦባማ ኬር” ማክተሙ ተበስሯል፡፡ 

ውሳኔውን ተከትሎ ሁለት የተለያዩ ስሜቶች ተንፀባርቀዋል፡፡ በአንድ ወገን ውሳኔው ያስቆጣቸው ዲሞክራቶች ውሳኔውን አሳፋሪ ሲሉት በአንፃሩ የሪፐብሊካኑ ደጋፊዎችን ደግሞ ጮቤ አስረግጧል፡፡

ዲሞክራቶች ይህ ውሳኔ በሚሊየን የሚቆጠሩ አሜሪካውያን አስተማማኝ የጤና መድህን እንዳኖራቸው ያደረገ ሲሉ ኮንነውታል፡፡

ከስድስት ሳምንታት በፊት መቋጫ ያላገኘው የቀድሞው የጤና መድህን ፖሊሲ የመተማመኛ ድምፅ ባለማግኘቱ ነበር ዳግም ድምፅ እንዲሰጥበት ተራዝሞ የቆየው፡፡

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በኋይት ሆነው ባሰሙት ንግግር እሳቸው “ኦባማኬር” ሲሉ የጠሩት የጤና መድህን ፖሊሲ ዕቅድ ሙሉ በሙሉ አክትሞለታል፤ ከዚህ በእጅጉ የተሻለውና በሪፐብሊካኑ የተነደፈው አማራጭ እቅድ በብዙ መልኩ የተሻለ እንደሆነም በልበ ሙሉነት ተናግረዋል፡፡

እቅዱ ወጪ የሚቀንስ፣ ውድድርን የሚያበረታታ፣ ለሁሉም አሜሪካውያን ጥራት ያለውና አዋጭ የጤና መድህን ዋስትና ለማቅረብ የሚሥችል እንደሆነመር በንግግራቸው ተብራርቷል፡፡   

 

በተጨማሪም እቅዱ ከዚህ ቀደም በባራክ ኦባማ ፖሊሲ ላይ የነበረውን "የጤና መድህን የማይገዙ ዜጎች ቅጣት ይጣልባቸዋል" የሚለውን ያስቀረ ነው ተብሏል።

ሪፐብሊካኖች ይህን ይበሉ እንጂ አዲሱ የጤና መድህን ረቂቅ ህግ ቀደም ሲል ከነበረው ብዙም የማይለይ ፤ የመድህን ዋስትና ክፍያውም ቢሆን  በጣም የተጋነነና አነስተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ምንም የማይፈይድ በሚል ከዲሞክራቶቹ ተደጋጋሚ ወቀሳ ሲሰነዘርበት ቆይቷል ፡፡

ሴናተር በርኒ ሳንደርስ በበኩላቸው አዲሱ እቅድ ባለፀጋ አሜሪካውያንን ብቻ የሚጠቅምና መካከለኛውና ዝቅተኛ ገቢ ያለውን አብዛኛውን ዜጋ ግን የጤና መድህን የነፈገ፣ በአንፃሩ ከፍተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል የታክስ ቅናሽ እንዲያገኝ በር የሚከፍት ነው በሚል ውሳኔውን አብጠልጥለውታል፡፡    

አዲሱ እቅድ ከቀድሞው የኦባማ ፖሊሲ ይዟቸው የሚቀጥላቸው ነጥቦች እንዳሉም የተወሳ ሲሆን ፤ ከእነዚህም መካከል እስከ 26 አመት እድሜ ያላቸው ዜጎች በቤተሰቦቻቸው አማካኝነት የጤና መድህን ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችለው ይጠቀሳል፡፡

ከዚህ ውጪ ረቂቅ የጤና መድህን ፖሊሲው ገቢራዊ  ሲደረግ ሀገሪቱን የጤና መድህን ሽፋን ከማስፋቱም በላይ የቀድሞ አሰራሮችን በአዲስ እንዲተኩ ያደርጋል ነው የተባለው፡፡

 ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኮንግረንሱ ጋር በመሆን የኦባማን የጤና ፖሊሲ በመሻር በአዲስ ህግ ለመተካት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ቀደም ሲል በኋይት ሀውስ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።( ምንጭ: ቢቢሲ)