ጀርመን የማህበራዊ ገጾችን በመጠቀም ጥላቻን የሚያሠራጩትን ዜጎችን የሚቀጣ ህግ አወጣች

ጀርመን  የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀም የጥላቻ ንግግሮችንና ለወንጀል የሚያነሳሱ ጽሑፎችንና ምስሎችን  የሚያሠራጩ ዜጎችን  የሚቀጣ ህግ አወጣች ።

ጀርመን በፈረንጆቹ 2017 ጥቅምት ወር ላይ የማህበራዊ ትስስር ገፆችን በመጠቀም የጥላቻ ንግግሮችን እና ለወንጀል የሚያነሳሱ ጽሑፎችንና ምስሎችን የሚያሰራጩ ዜጎችን በ24 ሰዓት ውስጥ  እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለማህበራዊ ድረ ገጽ ኩባንያዎች ውሳኔ አስተላልፋለች ።

አዲስ የወጣው ህግ አግባብነት የሌላቸው ጽሑፎችንና ምስሎችን የሚያስተላልፉ ኩባንያዎችን የማያስወግዱ እንደየ ጉዳዩ ቅለትና ክብደት ከ5 ሚሊየን  እስከ 57 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የገንዘብ እንደሚያስቀጣ  ዘግቧል፡፡

ይህ አሁን የወጣው አዲሱ ህግ በዓለም ላይ ካሉ ከባድ ህጎች መካከል አንዱ ነው ተብሏል፡፡

በጀርመን 30 ሚሊየን የሚጠጉ ተጠቃሚዎችን ያፈራው የፌስቡክ ኩባንያ በበኩሉ ህጉን እንደሚቀበለውና በኩባንያው በኩል የጥላቻ ጽሑፎችንና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማጥፋት እንደሚሰራ ተናግሯል ተብሏል፡፡

ኩባንያው አክሎም በማህበረሰቡ ላይ እየተጋረጠ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ማህበረሰቡ፣ መንግስት እና የኢንዱስትሪ ሠራተኞች በጋራ ካልሰሩ ህጉ ብቻውን ችግሩን አይፈታውም ብሏል ፡፡

በሌላ መልኩ የሰብአዊ መብትና የኢንዱስትሪ ቡድኖችና  ተወካዮች ህጉን አውግዘውታል፡፡

የሰብአዊ መብት ቡድኖቹና የኢንዱስትሪ ተወካዮቹ ይህ ህግ ኩባንያዎች ላለመቀጣት ሲሉ ወደ ቅድመ ምርመራ ማለትም ሳንሱር እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ነው ብለዋል፡፡

እኤአ በመስከረም 24 በሚካሄደው የጀርመን የፌደራል ምርጫ እስኪጠናቀቅ ህጉ ተግባራዊ አይሆንም ተብሏል፡፡