ፈረንሳይ ፣ ጀርመንና ጣሊያን በስደተኞች ጉዳይ ላይ ሊመክሩ ነው

የፈረንሳይ፣ ጀርመንና ጣሊያን የሀገር ውስጥ ሚኒስትሮች ስደተኞችን በተመለከተ በፓሪስ ሊመክሩ ነው፡፡

በውይይቱ በርካታ ስደተኞች መዳረሻቸውን ያደረጉባት ጣሊያንን እንዴት መርዳት እንደሚቻል ያነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የፈረንሳይ፣ ጀርመንና ጣሊያን ሚኒስትሮች እሁድ በፓሪስ ውይይት ያደርጋሉ፡፡ የውይይታቸው መሠረታዊ ጉዳይ ደግሞ አሁን አውሮፓን እያሳሰባት ስለመጣው ስደተኞችን በተመለከተ ነው፡፡

በርካታ ስደተኞች መዳረሻቸውን ባደረጉት የጣሊያን የባህር ዳርቻዎች ዙሪያ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ጣሊያንን አንዴት መደገፍ እንዳለባቸውም በውይይታቸው ያነሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጣሊያን ከአውሮፓ ኮሚሽን በተሰጣት ድጋፍ መሰረት አሁን የበርካታ ስደተኞች መዳረሻ የሆነውን ወደቧን ለመዝጋት ፍላጎት አላት፡፡ እናም ጣሊያን ይህን ውሳኔ ስትወስን ስደተኞቹ ሌላ የሜዲትራንያን ሀገራትን ምርጫቸው እንዲያደርጉ በማሰብ ነው፡፡

እኤአ ከ2014 ወዲህ  ከአምስት መቶ ሺህ በላይ ስደተኞች መዳረሻቸውን ወደ ጣሊያን አድርገዋል፡፡ ይህ ቁጥር በዘንድሮው ዓመት 82 ሺህ በጣሊያን መዳረሻዎችን  ያረጉ ስደተኞችን ጨምሮ ነው፡፡

የፈረንሳዩ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ጄራርድ ኮሎምብ እንዳሉት በዚህ ጉዳይ ለመምከር የጀርመንና የጣሊያን ሚኒስትሮችን ቀጥረዋል፡፡

ሮይተርስ እንደዘገበው ከሆነ ግን አሁን የሶስቱ ሀገራ መሪዎች የሚያደርጉት ውይይት ምንም ውጤት አያመጣም ብሏል፡፡ ምክንያም በቀጣይ ሳምንት የአውሮፓ አባል ሀገራት የሀገር ውስጥ ሚኒስትሮች በታሊን ኢስቶኒያ በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ ነው ቁርጥ ያለ ውሳኔ ሊተላለፍ የሚችለው፡፡

ይህን አስመልክቶ ባሳለፍነው ዓርብ መግለጫ የሰጡት የአውሮፓ ኮሚሽ ፕሬዝዳንት ጀን ክላውድ ጀንከር በተለይ ከጣሊያንና ግሪክ መሪዎች ጋር በቀጣይ በስደተኞች ጉዳይ ላይ ስለሚወሰዱ እርምጃዎችና ውሳኔዎች የኢስቶኒያው ጉባኤ ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አሁን ወደ አውሮፓ ለመግባት በርከት ያሉ ስደተኞች ፍላጎታቸውን እያሳዩ ነው፡፡

ጣሊያን ደግሞ ሁነኛ የስደተኞቹ መዳረሻ ናት፡፡ እንደውም የአውሮፓ ህብረት እንደሚለው ከጣሊያን ሌላ ሌሎች የአውሮፓ ህብረት ሀገራት የጣሊያንን ችግር ሊጋሩ ይገባል፡፡

የአውሮፓ ህበረት እንዳለው የባርሴሎናና የማርሴ ወደቦችም ስደተኞችን ለመታደግ በራቸውን እንዲከፍቱ የተጠየቁ የሀገራት ከተሞች ናቸው፡፡( ምንጭ: ሮይተርስ )