ሳውዲ አረቢያና አጋሮቿ ለኳታር ያስቀመጡትን የድርድር ቅድመ ሁኔታ በ 48 ሰዓታት አራዘሙ

ሳዑዲ አረቢያና አጋሮቿ ለኳታር ያስቀመጡትን የድርድር ቅድመ ሁኔታ ቀነ ገደብ ለተጨማሪ 48 ሰኣታት አራዘሙት፡፡

ኳታር በአገራቱ የተቀመጡትን የድርድር ቅድመ ሁኔታዎች ያጣጣለች ሲሆን፤ ሊያግባቡ በሚችሉ ጉዳዮች ዙርያ ለመወያየት ግን ዝግጁ ነኝ ብላለች፡፡

ከወር በፊት ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ አራት የአረቡ አገራት ከኳታር ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጣቸውን በይፋ አወጁ፡፡

‹‹ኳታር ፅንፈኛና አሸባሪ ድርጅቶችን ትደግፋለች›› የሚለው ደግሞ አገራቱ ግንኙነታቸውን ለማቋረጥ ለመገደዳቸው በምክንያትነት ይጠቅሳሉ፡፡

በኳታርና በአገለሏት አገራት መካከል የነገሰው አለመግባባትና መሻካር አሁንም በመፍትሔ አልባነት ቀጥሏል፡፡ ከ10 ቀን በፊት ከኳታር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ያቋረጡት አገራት ዶሃ ልታስተካክላቸውና ልትቀበላቸው የሚገቡ 13 የመደራደሪያ ነጥቦችን በማስቀመጥ ቀነ ገደብ አስቀመጡ፡፡

በአገራቱ ለኳታር እንደ ግዴታ ከተቀመጡት ውስጥም የአልጀዚራ የዜና አውታርን መዝጋት፣ ከኢራን ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጥ፣ በአገሪቱ ያለውን የቱርክ ወታደራዊ ጣቢያ መዝጋት፣ በምታራምደው የውጭ ፖሊሲ ግንኙነታቸውን ባቋረጡት አገራት ላይ ለደረሰው ኪሳራ ካሳ መክፈልን ይጨምራል ።

ከአገራቱ ወደ ኳታር ለሚሄዱ ዜጎች የዜግነት መብት እንዳይሰጥ፣ለሰጠቻቸውም የዜግነት መብታቸውን መግፈፍ፣ በአሜሪካ በአሸባሪነት የተፈረጁ ቡድኖችን መርዳትን ማቆም  የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ለዚህም በ10 ቀናት ውስጥ ኳታር አቋማን እንድታስታውቅ ቀነ ቀደብ ተቀምጦ ነበር፡፡

ኳታር አገራቱ ያቀረቡት ጥያቄዎች ውሃ የማይቋጥሩ ናቸው በማለት የቀረበውን ሃሳብ ባለመቀበል ቀነገደቡ ትናንት ተጠናቋል፡፡

በአገራቱ የተቀመጠው ቀነ ገደብ ትናንት መጠናቀቁን ተከትሎ እነ ሳዑዲ አረቢያ ዶሃ ጉዳዩን በደንብ እንድታጤነው ቀነ ገደቡን ለተጨማሪ 48  ሰዓታት ማራዘማቸውን ገልፀዋል፡፡

የአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከኳታሩ ኢሚር የተሰጣቸውን መልስ ዋና አሸማጋይ ለሆኑት ለኩዌቱ ኢሚር በአካል ለማድረስ ዛሬ ወደ እዛው ያቀናሉ ተብሏል፡፡

የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ መሃመድ ቢን አብዱራህማን ለድርድር የቀረቡትን ጉዳዮች አገራቸው እንደማትቀበለው ተናግረው  ሆኖም ግን ሊያግባቡ በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውን ነው የገለፁት፡፡

ከአራቱ አገራት አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ባለስልጣን ኳታር ከአሸባሪው ቡድን አይ ኤስ፣ ከአልቃይዳ እና በሊባኖስ ውስጥ ከሚንቀሳቀሰው ሂዝቦላ ጋርም ግንኙነት አላት በሚል በአገራቱ እየተወገዘች መሆኑን መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያናና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ባለስልጣናት ጋርም በጉዳዩ ዙሪያ በስልክ መወያየታቸው ታውቋል፡፡

ከአረቡ አገራት መገለል የደረሰባትን ኳታርን ኢራንና ቱርክ በምግብ አቅርቦትና በሌሎች መሰረታዊ ሸቀጦች በመደገፍ ከጎንሽ ነን እያሏት መሆኑን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡