የኢራቅ መንግሥት የሞሱልን ከተማ ከአይኤስ ነጻ ማውጣቱን አስታወቀ

የኢራቅ መንግሥት በአይ ኤስ ላይ ላይ ድልን በመቀዳጀት የሞሱል ከተማ ነፃ መውጣቱን  አስታወቀ፡፡

በአሸባሪው ድርጅት የተያዙ ሁለት ቦታዎችም በቅርብ ቀን ነፃ እንደሚወጡ የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጦሩና ለኢራቃውያን የምስጋናና የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ሞሱል ከአይ ኤስ ነፃ ብትወጣም ቡድኑን የመዋጋቱ ዘመቻ ግን ይቀጥላል ተብሏል፡፡

ታሪካዊቷ የሰሜን ኢራቅ ከተማ ሞሱል ከ2014 የፈረንጆቹ ዓመት ጀምሮ ነበር በአሸባሪው ድርጅት አይ ኤስ ቁጥጥር ሥር የወደቀችው፡፡

ፅንፈኛው አይ ኤስ የታሪካዊውና  የታላቁ አል ኑር መስጊድ መገኛ የሆነችውን ሞሱል በመቆጣጠር ነዋሪዎቹን ለእንግልትና ስደት ዳርጓል፡፡ አል ኑር መስጊድን ጨምሮ ሌሎች ታሪካዊና የከተማዋ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል፡፡

አሸባሪው ቡድን ሞሱልን መቀመጫ ከተማዬ ብሎ ከማወጅ ባለፈ በታላቁ አልኑር መስጊድ ፕሮፓጋንዳውን እስከ መንዛትም ደርሶ ነበር፡፡

የኢራቅ ጦር ከተማዋን ከፅንፈኛው ቡድን ለማስለቀቅ ከባድ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ጥረቱ ውጤት አምጥቶም ባለፈው ጥር ወር ምስራቅ ሞሱልን ማስለቀቁ ይታወሳል፡፡

ከሁለት ወር በፊት ደግሞ ምዕራባዊ ሞሱልን ከአይ ኤስ ለማስለቀቅ በአሜሪካ መራሹ ጥምር ኃይል በመታገዝ ትግሉ ተፋፍሞ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህም የአይ ኤስ አቅም እየተዳከመ ሞሱል ነፃ የምትወጣበት ጊዜ እየቀረበ መሆኑን የሚያሳዩ ውጤቶች ሊመዘገቡ ችለዋል፡፡

ባለፈው ወርሃ ጥቅምት 2016 የፈረንጆቹ ዓመት በከተማዋ ተሰማርቶ የነበረው ከስድስት ሺ በላይ የአይ ኤስ ሚሊሻዎች ቁጥር ወደ መቶዎች ወረደ፡፡ ጥምር ኃይሉ በአይ ኤስ የታገቱ በርካታ ንፁኃን ዜጎችንም ማስለቀቁ ተመልክቷል፡፡

የሽንፈት ዋዜማ ላይ መድረሱን የተረዳው አይ ኤስ በበኩሉ ትልቅ ውግዘትን ያስከተለውን 850 ዓመት ገደማ ያስቆጠረውን ታላቁን የአልኑር መስጊድን በማውደም ዕእኩይ ድርጊቱን ለዓለም ያንጸባረቀ  በመሆኑ ብዙዎችን አሳዝኗል ፡፡

ጥምር ኃይሉ አቅሙን በማጠናከር በአይ ኤስ ላይ ድልን በመቀዳጀት

ሞሱል ጨምሮ  ከሁለት ይዞታዎች ውጭ ከአይ ኤስ መዳፍ ነፃ መውጣቷ ነው የተነገረው፡፡

ድሉን ተከትሎ የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይደር አል አባዲ ሞሱል በመገኘት ለጦር ኃይሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጦር ሃይሉ በተጨማሪ በተገኘው ድል ለኢራቃውያንም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሞሱል ከተማ መደበኛ የሆነ ንግግር ባያደርጉም የሞሱል ነዋሪዎች አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡

አሁን በአይ ኤስ ቁጥጥር ሥር የሚገኙት ሁለት ቦታዎችን በቅርብ ቀን ውስጥ በማስለቀቅ በአገር ዓቀፍ ደረጃ ሞሱል ነፃ የወጣችበት የድል በዓል በድምቀት ይከራል ብለዋል-ጠቅላይ ሚኒስትር አባዲ፡፡

በአየር የሚሰነዘር ጥቃትና የተኩስ ልውውጥ በከተማዋ እየተሰማ እንደሆነም እየተነገረ ነው፡፡

ሞሱልን ማስለቀቅ አይ ኤስን ድባቅ መምታት ባለመሆኑ ፅንፈኛውን ቡድን የመዋጋቱ ጥረት በቀጣይ የሚጠናከር እርምጃ ነው ብላለች ኢራቅ፡፡