ደቡብ ኮርያ ያቀረበችው የእንወያየይ ጥያቄን ሰሜን ኮርያ ውድቅ አደረገችው

ደቡብ ኮርያ በወታደራዊ ጉዳዮች ዙርያ ለመወያየት ያቀረበችውን ጥያቄ ሰሜን ኮርያ ውድቅ አደረገችው፡፡  የፒዮንግያንግ የሴዑልን የእንነጋገር ጥያቄ አለመቀበል የሠላምን ጥሪ እንደ መግፋት ይቆጠራል ተብሏል፡፡

ደቡብ ኮርያ ባላንጣዋ ከሆነችው ሰሜን ኮርያ ጋር በወታደራዊ ጉዳዮች ዙርያ ለመወያየት እንደምትፈልግ በመግለፅ ከአምስት ቀን በፊት የእንነጋገር ጥያቄ አቅርባ ነበር፡፡

ሴዑል ጥያቄዋ በፒዮንግያንግ ተቀባይነት ካገኘ በመሪዎች ደረጃ በሁለቱ አገራት መካከል ከሶስት ዓመት በኋላ የተደረገ የመጀመሪያው ውይይት እንደሚሆንም ነበር ትልቅ ተስፋ የተጣለበት፡፡

የደቡብ ኮርያው ፕሬዚዳንት ሙን ጄ ኢን ከሰሜን ኮርያው አቻቸው ኪም ዮንግ ኡን ጋር በቅርበት በመነጋገርና በመመካከር በቀጣናው ሠላም እንዲሰፍን በተደጋጋሚ የሚገልፁትን ፍላጎት ውይይት እናድርግ  ጥያቄ  ተግባራዊ አድርገዋል ፡፡

ሴዑል ጎረቤቷ ፒዮንግያንግ ለጥያቄዋ አፋጣኝ ምላሽ እንድትሰጣት በመግለፅ አዎንታዊ ምላሽ እንደምታገኝም በተስፋ ስትጠባበቅ ቆይታ ነበር ፡፡

አሁን ታዲያ ከወደ ሰሜን ኮርያ የተሰማው ወሬ የሴዑልን ተስፋ ያጨለመ መሆኑ ነው የተነገረው፡፡ ፒዮንግያንግ የእንወያይ ጥያቄውን አልቀበልም በማለት ለመወያየት ፍቃደኛ አለመሆኗን አስታውቃለች፡፡

የፒዮንግያንግ እምቢተኝነት በኮርያ ባህረ ሠላጤ የነገሰውን ወታደራዊ ውጥረትን ለማርገብና በሁለቱ ኮርያዎች ድንበር አካባቢ መረጋጋት እንዲሰፍን በሚቻልበት ጉዳይ ዙርያ መፍትሔ ያመጣል በተባለው ውይይት ላይ ውሃ ቸልሷል፡፡

ፕሬዚዳንት ሙን ወደ ሥልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ከሰሜን ኮርያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሻሻል ያላቸውን ፍላጎት እንደሚገድብም ነው የተመለከተው፡፡

ፕሬዚዳንት ሙን በጀርመን በርሊን ባደረጉት ንግግር ለፒዮንግያንግ ያቀረቡት የእንነጋገር ጥያቄ ከዚህ ቀደሙ ጠንከርና ገፋ ያለ መሆኑን ነው ቢገልፁም ምላሹ ግን ያልተጠበቀ ሆኗል፡፡

ውይይቱ ቢሳካ ፒዮንግያንግ በተለያዩ ጊዜያት የምታደርገውን የሚሳኤል ሙከራ ተከትሎ ከፀብ አጫሪነት ድርጊቷ እንድትታቀብ ለሚጥሩ አካላትም ጥሩ እፎይታን ይሰጣል ተብሎ ነበር፡፡

የደቡብ ኮርያ መከላከያ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ሙን ሳንግ ጊዩን የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማሻሻልና በቀጣናው የነገሰውን ውጥረት ለማርገብ የላቀ ሚና የሚጫወተው የውይይት በር በሰሜን ኮርያ መዝጋቱ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

አሁንም ቢሆን ፒዮንግያንግ ጉዳዩን በደንብ አጢና ለሴዑል ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ እንድትሰጥ አሳስበዋል፡፡

ፒዮንግያንግ ለሴዑል ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ መንፈጓ የሠላም ጥሪን እንደመንፈግና ለሰላማዊ ውይይት ያላትን እምቢተኝነት በግልፅ እንደሚያሳይ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን የሰጡ አካላት መናገራቸው በዘገባው ተመልክቷል፡፡

በአገራቱ መካከል የሚደረገው ውይይት እኤአ በሐምሌ 21 2017 እንዲካሄድ ሴዑል በጥያቄዋ ማካተቷን የደቡብ ኮርያ ምክትል መከላከያ ሚኒስትር ሱ ቹ ሱክ መግለፃቸውን በመጠቆም ዘገባው  አስታውሷል፡፡

ሰሜን ኮርያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ማዕቀብ በመተላለፍ በተለያዩ ጊዜያት ከአጭር እስከ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ የሚሳኤል ሙከራዎችን አድርጋለች፡፡