በአረቡ አገራት ቀውስ ምክንያት ዶሃ ዲፕሎማሲያዊ ስጋት ላይ እንደምትገኝ ተገለጸ

የአረብ አገራት ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸውን ተከትሎ የዶሃ ዲፕሎማሲ ስጋት ላይ ይገኛል፡፡

ከዚህ ቀደም ከኳታር ጋር ጥሩ የሚባል የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው አገራት ስማቸው ኳታር ከተከሰሰችበት የሽብር ጉዳይ ጋር እንዳይነሳ የሰጉ ይመስል ዝምታን መርጠዋል፡፡

ኳታር ደግሞ ክሷን በማጣጣል ከባህረ ሰላጤው አገራት ጋር ያላት ግንኙነት እንዳይሻክር ፍላጎት ያላት መሆኗን ደጋግማ አስታውቃ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ሆኖም ወደሚፈለገው የመፍሔ አቅጣጫ ያልመጣው እና መቋጫ ያላገኘው የአረቡ አገራት ቀውስ አሁን ወደ መካከለኛው ምስራቅ የተሸጋገር ይመስላል፡፡

ቻይና ከባህረ ሰላጤው አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ረቡዕ እለት በአህመድ አልጃብር  የሚመራውን የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ልዑክን ቤጂንግ ተቀብላለች፡፡ ከአንድ ቀን በኋላም  የኳታሩ ውጭ ጉዳይ ሼክ ሞሐመድ ቢን አብዱራህማን አል ታኒ ቻይና ገብተዋል፡፡

እንደ ሺኗ ቻይና አገራቱን የመዳኘት ሚናዋን ለመወጣት የምታደርገው ጥረት ነው ተብሏል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዋንግ ዪ በአረቡ አገራት እና በመካከለኛው ምስራቅ ለአመታት የዘለቀው ግንኙነት የሚጠናከርበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ቻይና ደግሞ በዚህ ግንኙነት መካከል የአገራቱን ቅራኔ ለመፍታት ትጥራለች ነው የተባለው፡፡

ይህ የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ ተግባር ነው እየፈፀምን ያለነው ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፡፡ የኳታሩ አቻቸው በበኩላቸው የቻይናን ጥረት አድንቀዋል፡፡

 ቻይና አለማቀፍ ህጎች እንዲከበሩ እና በድርድሩ የኳታር ድምፅ እንዲሰማ መንገድ እንደምትከፍት ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ከቻይና ጋር የመከሩት የሳዑዲው ሱልጣን አህመድ አልጃብር ቤጂንግ በባህረ ሰላጤው አገራት መካከል ታሪካዊ አሻራዋን ለማሳረፍ እየጣረች ነው ብለዋል፡፡ በቤጂንግ እና ዶሃ መካከል እኤአ ከ 2014 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተለያዩ የስምምነት ሰነዶች ተፈርመዋል፡፡

ቱሪዝም አገራቱን በኢኮኖሚ የሚያስተሳስር እና ግንኙነታቸውም በስትራቴጂ እንዲመራ እና ዘለቄታ እንዲኖረው ፍኖት የጠረገ ነው ተብሏል፡፡( ምንጭ: አልጀዚራ ፣ ዥንዋ)