በስደተኞች ጉዳይ ላይ የሚመክር ጉባኤ በፈረንሳይ ሊካሄድ ነው

ፈረንሳይ በስደተኞች ጉዳይ ላይ ዘላቂ የመፍትሔ መሰረት ያደረገ ውሳኔ የሚተላለፍበትን ጉባኤ በመጪው ሳምንት ልታካሂድ ነው፡፡

በጉባኤ የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ የስደተኞች መዳረሻ እና መተላለፊያ የሆኑ አገራት መሪዎችም ይገኛሉ ተብሏል፡፡

የአውሮፓ ህብረት አገራት መሪዎች ከአፍሪካ አቻዎቻቸው ጋር መቋጫ ባጣው በስደተኞች ጉዳይ በመጪው ሰኞ በፓሪስ ሊመክሩ ነው፡፡

ጣሊያን በስደተኞች ላይ የያዘችውን አምባገነናዊ አቋም እና ከሰሞኑ እየወሰደች ያለውን እርምጃ ተከትሎ አለማቀፉ ማህበረሰብ ማውገዙ መነሻ የሆናቸው የስደተኞቹ መዳረሻ አገራት መሪዎች በቀጣይ መፍትሔዎች ዙሪያ ለመምከር ቀጠሮ ይዘዋል፡፡

የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ባዘጋጁት በዚህ ጉባኤ ላይ የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንሄላ መርክል፣ የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪያኖ ራጆይ፣ የጣሊያኑ አቻቸው ፓውሎ ጀንቲሎኒ እና የአውሮፓ ህብረት ውጭ ጉዳይ ፌደሪካ ሞገሪኒ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተረጋግጧል፡፡

አፍሪካን ወክለው የሚገኙት የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ማሃመዱ ኢሶፉ፣ የቻዱ ፕሬዝደንት ኢድሪስ ዴባይ እና ከሊቢያም በተመሳሳይ የሚሳተፉበት ነው ተብሏል፡፡

ከአብዛኛው የአፍሪካ አገራት የሚወጡት ስደተኞች ወደ አውሮፓ ግዛቶች ለማምራት እንደመሸጋገሪያ የሚጠቀሙባቸው እንደ ሊቢያ ወዳሉ አገራት የሚገቡት በረሃማዎቹን ኒጀር እና ቻድን በእግራቸው አልያም ተደራርበው በሚጫኑባቸው ተሽከርካሪዎች አቋርጠው ነው፡፡

ታድያ ስደተኞቹ እግራቸው የአውሮፓን ምድር ሳይረግጥ በእነዚሁ አገራት እንዳሉ የጥገኝነት ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ የሚያስችል አሰራር እንዲዘረጋ ጣሊያን እና ስፔን ያቀረቡት ሀሳብ ከዚህ ቀደም በአፍሪካዎቹ የስደተኞች መሸጋገሪያ አገራት ተቀባይነት ሳያገኝ ውድቅ ተደርጓል፡፡

በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ወደ ፈረንሳይ ሲጓዙ ከነበሩት ስደተኞች እስካሁን ባለው መረጃ ከ2ሺ 4መቶ በላይ ስደተኞች የባህር ሲሳይ ሆነው እንደቀሩ ዓለማቀፉ የስደተኞ ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡

ይህንን መሠረት አድርገው የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ባለፈው ወር ስደተኞቹን ሊቢያ ላይ ማስቀረት ስለሚቻልበት ሁኔታ አንድ ውሳኔ ላይ መድረስ አለብን ማለታቸውም ይታወሳል፡፡ ታዲያ የአሁኑ ጉባኤ ለዚህ መልስ የሚሰጥ ይመስላል፡፡

አብዛኞቹ የአፍሪካ ስደተኞች በኢኮኖሚ ምክንያት አገራቸውን ለቀው የሚወጡ እንደመሆናቸው እንደሌሎቹ በፖለቲካ አልያም ሰላምና መረጋጋትን አጥተው እንደሚንገላቱቱ በአውሮፓ አገራት ተቀባይነትን ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡

ስለዚህ ባህርን ለመሻገር ሲሉ ከሚደርስባቸው ሞት እና ተሻግረውም ለስቃይ ከመዳረጋቸው በፊት ድንበር ላይ ባሉ የአፍሪካ አገራት ውስጥ እንዳሉ የጥገኝነት ጥያቄያቸውን ማቅረብ እንዲችሉ ማመቻቸት የጉባኤው ዓላማ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ይህ ደግሞ በአውሮፓ አገራት ይደርስ የነበረውን መጨናነቅ በእነዚሁ አገራት ለማስቀረት ያለመ ነው በማለት እቅዳቸውን ሃላፊነት ላለመውሰድ የሚያደርጉት ግፊት ነው ሲሉ የሚነቅፏቸውም አልጠፉም፡፡

እንደ ዓለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት መረጃ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ ብቻ ከ120ሺ በላይ ስደተኞች የአውሮፓን ምድር ረግጠዋል፡፡

ይህ አሃዝ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው 261 ሺ ስደተኞች ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በግማሽ የወረደ ነው፡፡ መረጃውን ከሲ ኤን ኤን ተመለከትን፡፡