የአውስትራሊያ ከ70 በመቶ በላይ ቤቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የታዳሽ ኃይል ይፋ ተደረገ

ታዳሽ ሃይልን በመጠቀም በሃገሪቱ ከሚገኙ ቤቶች ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ መኖሪያ ቤቶችን የኤሌክትሪክ ሃይል ለማቅረብ የሚያስችል ግኝት ላይ መድረሱን የአውስትራሊያ ታዳሽ ሃይል ተቋም ገለጸ፡፡

ተቋሙ አሁን ይፋ ያደረገው አዲስ ግኝት የ70 በመቶውን የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎት ይሸፍናል ነው የተባለው፡፡

ተቋሙ ባሳለፍነው ሰኞ በሰጠው መግለጫ የሃይል ምንጩ በግንባታ ስራ ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም 90 በመቶ የሚሆነውን የሃገሪቱን የሃይል ፍላጎት ይሸፍናልም ብሏል፡፡

ተቋሙ ከተያዘው የፈረንጆቹ አመት ሰኔ ወር አንስቶ ግኝቱን ተግባራዊ ማድረግ የጀመረ ሲሆን፥ 31 በመቶውን የኤሌክትሪክ ሃይል ከነፋስና አስራ ስምንት በመቶ የሚሆነውን ደግሞ ጣራ ላይ ከሚሰቀል የጸሃይ ሃይል ማጠራቀሚያ በመውሰድ አርባ በመቶውን ሃይል በመሸፈን ወደስራ ገብቷል፡፡

ትሪስታን ኤዲስ የተባለ አንድ የታዳሽ ሃይል ባለሙያ እንደገለጸው አውስትራሊያ የታዳሽ ሃይልን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎትን ለመሸፈን የምታደርገው ጥረት ሊደነቅ ይገባል ብሏል፡፡

ከጸሃይ ብርሃን እና ከነፋስ  የሚገኘው የአሌክትሪክ ሃይል ለኢንቨስትመንት ዘርፉ መስፋፋት ጉልህ ሚና ይኖረዋልም ብሏል ኤዲስ፡፡

እኤአ በ2020 የአውስትራሊያ ኢንቨስትመንት ከአጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎቱ ውስጥ ሃያ በመቶውን በዚሁ የታዳሽ ሃይል የመሸፈን እቅድ እንዳለውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

እስከ 2017 መጨረሻ ድረስ ከስምንት ሺህ ስምንት መቶ በላይ የነፋስ ሃይልን ወድ ኤሌክትሪክ ኃይልነት የሚቀይሩ ማማዎች እና ከአንድ መቶ ሃምሳ ሺህ በላይ የጸሃይ ሃይል ማጠራቀሚያ መሳሪያዎች ተከላ ስራ ይሰራልም ነው የተባለው፡፡

እነኚህ የሃይል አማራጮች አውስትራሊያዊያን በቀጣዮቹ አስር አመታት ለኤሌክትሪክ ሃይል ፍጆታ ከሚያወጡት ገንዘብ ላይ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላሩን ይቀንስላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡( ሲጂቲኤን)